የህወሃት ከሃዲ ቡድን መወገድ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ያረጋገጠ ነው...የሃገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
የህወሃት ከሃዲ ቡድን መወገድ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ያረጋገጠ ነው...የሃገር ሽማግሌዎች
ባህር ዳር፣ ህዳር 25/2013(ኢዜአ ) የህወሃት ከሃዲ ቡድን መወገድ የኢትዮጵያን አንድነት እንደገና በፀና መሰረት ላይ ያስቀመጠ ድል መሆኑን የጎንደር ከተማ የሃገር ሽማግሌዎችና ነዋሪዎች ገለፁ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ነዋሪዎቹ ሃገሪቱን ላልተፈለገ ቀውስ፣ የሃብት ውድመትና ለሰው ህይወት መጥፋት የዳረገው ጁንታው ህወሓት ለህግ የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የከተማው የሃገር ሽማግሌ አቶ ባየ በዛብህ እንዳሉት የህወሃት ቡድን በሃገሪቱ ንፁሃን ዜጎች ላይ ያደረሰው በደል የታሪክ ጠባሳ ነው።
በጁንታው የጥፋት ሴራ ዜጎች እንዳይተማመኑ፣ እርስ በእርስ መከፋፈል፣ ወንድም በወንደሙ ላይ የጭካኔ ግድያ፣ ዘርን መሰረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ዝርፊያና መሰል ውስብስብ ችግሮች መከሰታቸውን ተናግረዋል።
ሃገርን ለከፋ ችግር በማጋለጥም ልጆቿ ተስፋ በማጣት ለስደት የተዳረጉበት አስከፊ ወቅት እንደነበር ያስረዱት አቶ ባየ፤ እርሳቸውም በግላቸው ለሁለት ዓመታት ያህል ማንም ሰው እንዳያነጋግራቸው ሆነው በእርስ ቤት መሰቃየታቸውን አስታውሰዋል።
"ይደርስ በነበረው ጥቃት፣ በደልና አፈና የተማረሩ የጎንደርና አካባቢው ወጣቶች በተደጋጋሚ ቁጣቸውን በሰልፍ የገለፁ ቢሆንም የህወሃት ቡድን በበለጠ የጭካኔ በትሩን አሳርፏል” ብለዋል።
“በክፋትና በሴራ ተወልዶ ያደገው ይህው ቡድን ከለውጡ እራሱን በማግለል ዳግመኛ ኢትዮጵያን በደም ጎርፍ ሊያጥባት በሃገር ውስጥና በውጭ ተባብሮ ሃገሩላይ ዳግም ክህደት ፈፅሟልም” ብለዋል።
የግፍ ፅዋ ሞልቶ የፈሰሰው የህወሃት የጥፋት ቡድን የሃገሪቱን አርማ የሆነውን መከላከያን በመንካት ፍፁም ጭካኔውን ማሳየቱን ጠቅሰው፤ ነገር ግን የለኮሰው እሳት ዳግም እንዳይነሳ መደረጉ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያውያን በሰላም ይኖራሉ ያሉት አቶ ባየ፤ የጥፋት ቡድኑ ከያለበት ተለቃቅሞ ለህግ መቅረብ እንዳለበትም ገልፀዋል።
''በጎንደርና አካባቢው ወጣቱ ወጥቶ መግባትም ሆነ ሰርቶ መብላት ከማይችልበት ደረጃ አድርሶት ነበረ'' ያሉት ደግሞ አቶ በላይነህ አርአያ ናቸው።
የስግብግቡ ጁንታ ቡድን የሃገሪቱን የአይደፈሬነት ታሪክ ለማበላሸት መሞከሩን ጠቅሰው፤ “ጀግናው መከላከያ ሰራዊት በወሰደው አጸፋዊ እርምጃ ከነክፉ ሃሳቡ ወደ መቃብሩ እንዲወርድ አድርጎታል”ብለዋል።
“የመከላከያ ሰራዊቱ በቁጭት ተነስቶ በተገቢው ሰዓትና በተገቢው ቦታ ብዙ መስዋትነት ሳይከፈል የሽፍታው ቡድን አከርካሪውን ሰብሮ መጣል መቻሉ ለኢትዮጵያ እንደ አዲስ መወለድ ነው” ብለዋል።
የጥፋት ቡድኑን ወደ ህግ የማቅረቡ ስራ በተደራጀ አግባብ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰው፤ የትግራይን ህዝብ መልሶ በማደራጀትም ከወዲሁ ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ሌላው የከተማው ነዋሪ መምህር ይሄነው አላምረው በበኩላቸው “ህወሃት የጎንደርና አካባቢው ህዝብ በልማት እንዳይጠቀም ከማድረጉ ባለፈ ተጨቁኖና ተረግጦ እንዲኖር አድርጎታል”ብለዋል።
“ቡድኑ የሃገር ደጀን የሆነውን መከላከያ ሰራዊት በመውጋት በዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ አስነዋሪና አዋራጅ ታሪክ የፃፈ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
“ማንም አይደፍረኝም ሲል የነበረውን የህወሃት ጁንታ ቡድን ሰራዊቱ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት መደምሰሱ ለሃገሪቱ ዘላቂ ሰላምና እድገት ወሳኝ ምዕራፍ” ነው ብለዋል።
በተደረገው ህግ የማስከበር ዘመቻ እስከ መጨረሻው በመጓዝ አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።