ቀጥታ፡

በትግራይ የሰላማዊ ዜጎች ኑሮ እንዳይቃወስ ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ ገለፁ

ህዳር 24/2013 (ኢዜአ) በትግራይ እየተካሄደ ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻ የሰላማዊ ዜጎች ኑሮ እንዳይቃወስ ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ ገለፁ።

አምባሳደሩ ከፍራንስ 24 የቴሌቪዝን ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስረዱት፤ በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የህግ ማስከበር ተግባሩን አስገዳጅ አድርጎታል።

“በትግራይ ክልል ያሉ ሰላማዊ ዜጎች አፋጣኝ ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው” ብለዋል።

የመከላከያ ሰራዊት በተቆጣጠራቸው ቦታዎች የሚኖሩ ዜጎች ድጋፍ ማግኘት ስለመጀመራቸው ያነሱት አምባሳደሩ፤ የህወሃት ቡድን በመሰረተ ልማት ላይ ውድመት ማድረሱ በሚፈለገው ልክ ለመስራት እንዳላስቻለ አብራርተዋል።

አምባሳደሩ እንደተናገሩት፤ የእርዳታ ስርጭትን በሚመለከት ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ከሌሎች አጋሮች ጋር እየሰራች ነው።

የህግ ማስከበር ዘመቻው አሁን ላይ የተጠናቀቀ በመሆኑ የመንግስት ትኩረት ዜጎች ወደ አገራቸው ተመልሰው ወደ ቀደመ ኑሯቸው እንዲመለሱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የህወሃት ቡድን በትግራይ ክልል ያሉ ከተሞችና የመሰረተ ልማት አውታሮች ሆነ ተብለው እንዲፈርሱና አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጎ መሄዱ የዜጎችን ኑሮ አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግረዋል።

የህወሃት ቡድን በሰሜን እዝ ያሉ የመከላከያ አባላት ላይ የከፈተው ጥቃትና የወታደሮች ግድያ ለደረሰው ምስቅልቅል ምክንያት መሆኑን ያብራሩት አምባሳደር ሄኖክ፤ “መንግስት ህግ የማስከበርና የዜጎችን የተረጋጋ ህይወት የማስቀጠል ሃላፊነት ስላለበት ወደ ዘመቻው ገብቷል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም