የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮቪድ-19 ክትባትና ሌሎች መድኃኒቶችን ለማጓጓዝ ከአሊባባ ግሩፕ ጋር ተስማማ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮቪድ-19 ክትባትና ሌሎች መድኃኒቶችን ለማጓጓዝ ከአሊባባ ግሩፕ ጋር ተስማማ
አዲስ አበባ ህዳር 24/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮቪድ-19 ክትባትን ጨምሮ ሌሎች መድኃኒቶችን ለማጓጓዝ ከአሊባባ ግሩፕ ጋር ተስማማ።
ክትባቱ ደረጃውን በጠበቀ ማቀዝቀዣ ተቀምጦ በሣምንት ሁለት ጊዜ በሼንዘን ወደ አፍሪካ፤ እንዲሁም በአዲስ አበባና በዱባይ አድርጎ ለመላው ዓለም እንደሚሰራጭ ተገልጿል፡፡
ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር በቻይና የመድኃኒት ሎጂስቲክስ አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ ከሰጣቸው አራት አየር ማረፊያዎች የሼንዘን አየር ማረፊያ አንዱ ነው፡፡
ኬኒዎስ ስማርት ሎጂስቲክስ ኔትወርክ የአሊባባ ግሩፕ አካል ሲሆን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር የመድኃኒት ማጓጓዝ አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል፡፡
በቻይና የመጀመሪያ የሆነው ድንበር ተሻጋሪ የመድኃኒት ማጓጓዝ አገልግሎት በመደበኛነት የሚተገበር ሲሆን የኮቪድ-19 ክትባት ጨምሮ የማቀዝቀዣ ቁጥጥርን በመተግበር ሌሎች መድኃኒቶችን ለማጓጓዝ ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡
የማጓጓዝ ተግባሩ ጥብቅና ውጤታማ በሆነ የትራንስፖርት አስተዳደር በመታገዝ እንደሚተገበርም ተገልጿል፡፡
በማጓጓዝ ሂደቱ የሚሳተፉ የበረራ አባላት የአየር መቆጣጠሪያ መሳሪያ የሚይዙ ሲሆን በዚህም የበረራውን ተለዋዋጭ የአየር ሙቀት በቦታው በመሆን መከታተል ይችላሉ ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት ተርሚናል ባለው ማቀዝቀዣና መሰል አገልግሎት መስጫዎች ለስራው ብቁ መሆኑም ተገልጿል፡፡
"ኬኒዎስ ግሎባል ሎጂስቲክስ ኔትወርክ በ200 አገራት የሚሰራ ሲሆን የተቀላጠፈና የተሳሰረ የሎጂስቲክስ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጀት" ነው ሲሉ የኬኒዎስ ዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ስራ አስኪያጅ ጀምስ ዛሆ ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ትስስሩ የተለያዩ መድኃኒቶችና የኮቪድ-19 ክትባትን ለማሰራጨት ያስችለናልም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም "የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጎናጸፈውን አኩሪና ዓለም አቀፋዊ ስኬት መሰረት በማድረግ ከጥቂት ወራት በፊት ጀምሮ የኮቪድ-19 የግል መከላከያ ቁሳቁሶችን ማጓጓዙን አታውሰዋል።
አሁንም ባገኘው ስኬት በመታገዝ የኮቪድ-19 ክትባት ለመላው ዓለም ያሰራጫል ነው ያሉት፡፡
አቶ ተወልደ "የኮቪድ-19 ክትባት መሰራጨት ከሚጀምርበት ቅፅበት አንስቶ ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ግንባር ቀደም በመሆን ክትባቱ ለመላው ዓለም እንዲዳረስ እናደርጋለን" ብለዋል፡፡