ቀጥታ፡

በትምህርት ቤቶች ኮሮናን ለመከላከል የዘርፉ አመራሮች የሚጠበቅባቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተጠቆመ

ሀዋሳ ህዳር 24 / 2013 (ኢዜአ ) በደቡብ ክልል ትምህርት ቤቶች ኮሮናን በመከላከል በኩል እየተስተዋለ ያለውን መዘናጋት ለማስቀረት የዘርፉ አመራሮች የሚጠበቅባቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተጠየቀ ፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ በአካባቢው እየተካሄደ ባለው የመማር ማስተማር ሥራ ላይ በተደረገው የድጋፍና ክትትል ግብረ መልስ እንዲሁም የአስር  ዓመቱን የዘርፉ መሪ ዕቅድ ዙሪያ በሀላበ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ማሄ ቦዳ በመድረኩ እንደገለጹት፤ በክልሉ የመማር ማስተማር ሂደቱን ዳግም ለማስጀመርና ኮሮናን መከላከልን መሰረት ባደረገ መልኩ ለማስቀጠል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተከናውኗል።

መንግስት ከሚያቀርበው  የመከላከያ ቁሳቁሶችና ግብአቶችን ባሻገር ህብረተሰቡን በማነቃነቅ ሰፊ ድጋፍ መገኘቱንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከ12 ሺህ በላይ አዳዲስ መማሪያ ክፍሎች በህብረተሰቡ ትብብር መገንባታቸውን አስረድተዋል፡፡

የተማሪ መቀመጫዎች፣ የእጅ መታጠቢያዎች፣ መፀዳጃዎች፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች በመንግስትና ህዝቡ ትብብር እንዲሟሉ መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ትምህርት ሚኒስቴር ያስቀመጠውን መመዘኛ ማሟላታቸውን በየአካባቢው በተዋቀሩ ግብረ-ኃይሎች የተረጋገጡ ትምህርት ቤቶች ማስተማር መጀመራቸውን ጠቁመው፤ማስተማር ከጀመሩት ትምህርት ቤቶች ውስጥ 170 የሚሆኑት ያሉበት ሁኔታ መገምገሙን ገልጸዋል።

በግምገማውም  በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለው ኮሮናን የመከላከል ሥራ መዘናጋት እየተስተዋለበት እንደሆነ  የቢሮው ኃላፊው አመልክተዋል።

በተለይ ተማሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እያላቸው በአግባቡ በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ መጠቀም ያለመፈለግ ዝንባሌ መታየቱን አስረድተዋል።

ይህንን መዘናጋት ለማስቀረት የትምህርት አመራሩ ሁኔታውን በቅርበት እንዲከታተል፣ እንዲደገፍና ግንዛቤ ለማሳደግ መስራት እንዳለበት ጠቁመው ለዚህም አቅጣጫ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ንዳ በበኩላቸው፤ በቅድመ ዝግጅት ወቅት ከመንግስት የተጠበቀው ጭንብል በወቅቱ ባለመድረሱ  ከወላጆች ጋር በመነጋገር እንዲያሟሉ መደረጉን ገልጸዋል።

ሆኖም  ተማሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል  ከትምህርት ቤት መግቢያ በሮችና መማሪያ ክፍሎች በስተቀር በአግባቡ እንደማይጠቀሙ አመልክተዋል፡፡

በተማሪዎች ዘንድ የሚስተዋለው መዘናጋት ከማህበረሰቡ ዝንባሌ የመነጨ እንደሆነና ይህንን ማስቀረት ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ከጤና መምሪያና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር  የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መንግስቱ ግርማ  በትምህርት ቤት ውስጥ የሚታየው መዘንጋት ጭንብል  ያለመጠቀም ብቻ ሳይሆን ውሀና ሌሎች የንፅህና መጠበቂያ ግብዓት ተከታትሎ ያለማሟላት ችግርም እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት በየደረጃው ባለ ግብረ-ኃይል አማካይነት ጥረት እደረጉ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

በምክክር መድረኩ  የክልል፣ የዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ትምህርት ጽህፈት ቤት ሀላፊዎች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም