ቀጥታ፡

የህወሃት ጁንታ ቡድን ሽንፈት ለዘላቂ የሰላም መረጋገጥ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል- ምሁራን

ባህርዳር፣  ህዳር 23/2013 (ኢዜአ) የህወሃት ጁንታ ሽንፈት የኢትዮጵያ ህዝብ ከነበረበት ሰቆቃና የሰላም እጦት በዘላቂነት ለማውጣት የሚያስችል አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ሲሉ በባህርዳር ዩንቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

በዩንቨርሲቲው የታሪክ ተመራማሪና መምህር ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ ለኢዜአ እንደገለጹት በህወሃት ጁንታ ሽንፈት ያመጣውን ድል ዳር ለማድረስ የመንግስትና የመላ ህዝቡ ንቁ ተሳትፎ ያስፈልጋል።

ይህም የትግራይ ወገኖችን ይደርስባቸው ከነበረው ችግር ፈጥኖ ለማውጣት እንዲቻል ቡድኑ በሽሽቱ ወቅት ያወደማቸውን መሰረተ ልማቶች በመጠገንና መልሶ በማልማት መሳተፍ ተገቢ ነው ብለዋል።

“ከዚህ ባለፈ እንደ ሃገር እንዴት ወደዚህ አስከፊ ሁኔታ ልንገባ እንደቻልን ጥናት በማካሄድ በቀጣይ በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥም በመመርመርና የቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ መስራት ይገባል”ብለዋል።

የህወሃት ጁንታ ቡድን የመረጠው የፖለቲካ አካሔድ ለ27 ዓመታት በስልጣን ላይ ቢያቆየውም ከዝርፊያና ሰቆቃ በስተቀር ለሌላው ህዝብ ያስገኘለት ነገር ስለሌለ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ጠንካራ ስራ እንደሚፈልግ ተናግረዋል።

"አእምሮ ያለው ህዝብ በዚህ መንገድ መቀጠል የለበትም" ያሉት ፕሮፌሰር ሹመት መላ ህዝቡ የተሻለውን መንገድ በመፈለግ፣ በመምረጥና በመተግበር ከተደቀነበት አደጋ መውጣት እንዳለበት መክረዋል።

ጥቂቶች በሚነዙት መርዛማ ቅስቀሳ በመገፋፋት ለጥፋት በመነሳሳት ወገኑ ላይ ጉዳት የሚያደርስ አካል ከዚህ በኋላ እንዳይኖር ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

“ዘላቂ የሀገር አንድነትን ለማስጠበቅ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጥ ለማስመዝገብ ህዝቡ የበሰለና ከተሞክሮው የተማረ መሆን አለበት”ብለዋል።

"አባቶቻችን ሁሉም ህዝብ ተስማምቶ፣ ተፈቃቅሮና ተጋምዶ እንዲኖር የተሻለውን መንገድ መርጠዋል” ያሉት ምሁሩ “እኛ ደግሞ ከነሱ በመሻል በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር መስራት አለብን” ብለዋል። 

በባህርዳር ዩንቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር እምቢአለ በየነ በበኩላቸው የህወሃት ጁንታ ቡድን ሽንፈትን ተከትሎ የሚስተዋሉ ብዥታዎችን ለማጥራት ተከታታይ ውይይት ማካሄድ አስፈላጊ ነው።

ውይይቱም ትግራይ ክልል የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ተወላጆችን በማሳተፍ ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሄ ማምጣትና የለውጡ አካል ማድረግ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

የትግራይ ክልልን በጊዜያዊ ሁኔታ በራሱ ሰዎች ከማስተዳደር ባለፈ አካባቢው ተረጋግቶ በኢትዮጵያ ዘላቂ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲመጣ በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ባለፉት 27 ዓመታት ያ ሁሉ ዝርፊያ፣ ጭፍጨፋና በደል ሊከሰት የቻለው በህብረተሰቡ ታጋሽነትና የተለያዩ የጁንታው መጠቀሚያ ተቋማት ድጋፍ በማድረጋቸው የመጣ ውጤት መሆኑንም ገልጸዋል።

“አሁን በሃገር ደረጃ ያጋጠመን ቀውስ የአንድ የፖለቲካ ድርጅት የስራ ውጤት ብቻ ሳይሆን የሁላችንም የክትትልና የቁጥጥር ማነስ የጋራ ድምር ስህተት ነው”ብለዋል። 

እስከ አሁን በሀገርና በህዝብ ላይ ከተፈጸመው ጥፋት ትምህርት በመውሰድም በቀጣይ መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ በማድረጉ ረገድ መንግስት ከህብረተሰቡ፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና መገናኛ ብዙሃን ሃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም