ቀጥታ፡

የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የስራ እንቅስቃሴን የመስክ ምልከታ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23/2013(ኢዜአ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የስራ እንቅስቃሴን የመስክ ምልከታ አድርጓል።

ቋሚ ኮሚቴው ክትትል፣ቁጥጥርና ድጋፍ ለማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን የተለያዩ ማእከላትን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክቷል።

የመስክ ምልከታው ተቋሙ የሚሰጠው አገልግሎትና በእቅድ የተያዙ ፕሮጀክቶች ያለቡትን ደረጃ በመገምገም በታዩ ክፍተቶች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ለማሳሰብ መሆኑም ተገልጿል።

ቋሚ ኮሚቴው ለናሙና በተመረጡ የቅድመና ድህረ ክፍያ አገልግሎት ማእከላት ምልከታውን አድርጓል።

የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ገበየሁ ሌካሳ በሰጡት ማብራሪያ የቅሬታ ምንጭ በመሆን የዘለቀውን የሀይል መቆራረጥ ችግር ለመፍታት የመካከለኛ መስመር ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል።

ተቋሙ የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች እስኪያጠናቅቅ ድረስ ተራ በማውጣት ስለሚሰራ የሀይል መቆራረጥ ሊያጋጥም እንደሚችልም ጠቁመዋል።

የቅሬታ ምንጭ የሆነውን የመልካም አስተዳደር እና የስነ ምግባር ችግር ለመፍታት ኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ (ERP) የተባለ ስርአት በመዘርጋት በሰራተኛው እለታዊ የስራ እንቅስቃሴ ላይ ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላትም ተቋሙ ቴክኖሎጂን በመደገፍ፣ በክፍያ፣ በንብረት አያያዝና ቁጥጥር ላይ እየሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ 36 የሚሆኑ አገልግሎት መስጫ ማእከላት ቢኖሩም በአንድ ማእከል ላይ ጭንቅንቅ የሚበዛው በቂ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ባለመሰጠቱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጥገና እና የሲስተም መቆራረጥ ህብረተሰቡን ላልተገባ እንግልት በመዳረጉ ተቋሙ ችግሮቹን  ከሚመለከተው አካል ጋር በመተጋገዝ ይፈታል ብለዋል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎችም መተግባር እንዳለባቸው ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ አስተያየቶችን እንደ ግብአት በመውሰድ በቀጣይ አገልግሎቱን ለማሻሻል እንደሚሰራ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም