ቀጥታ፡

ተቋሙ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅበታል- ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 23/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የአገልግሎት አሰጣጡን ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተደራሽ ማድረግ እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ። 

በምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተቋሙን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ገምግሟል።  

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በህዝብ ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎች ላይ ጥያቄና አስተያየቶችን ሰንዝረዋል።    

በዜጎች ላይ የሚደርሱ አስተዳራዊ በደሎችን በተመለከተ በሩብ ዓመቱ ከቀረቡ አቤቱታዎች 201 ተቀባይነት ያገኙ፤ ከ2012 ዓ.ም ሩብ ዓመት የዞሩ 273 በአጠቃላይ 474 መዝገቦች ውስጥ 206 መዝገቦች ምርመራ አለመጠናቀቁ ተገልጿል።    

ተቋሙን የማይመለከቱ አቤቱታዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ያነሳው ምክር ቤቱ አገልግሎት ፈላጊዎች ግንዛቤ ይዘው አቤቱታ እንዲያቀርቡ በማድረጉ ረገድ ብዙ ሊሰራ እንደሚገባም ነው የተገመገመው።   

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አቡ ቢርኪ እንደተናገሩት፤ የመገናኛ ብዙሃንና መረጃ ነጻነት አዋጅን ሁሉም ተቋማት ተግባራዊ እንዲያደርጉ የተጀመሩ ስራዎች ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል።  

የመፍትሄ ሀሳብ የተሰጠባቸው መዝገቦችን ተከታትሎ ከማስፈጸም አኳያ 183 መዝገቦች ተከታትሎ ለ73 መዝገቦች ብቻ መፍትሄ መሰጠቱ ክፍተት እንዳለ የሚያመለክት መሆኑን ገልጸዋል።

ልዩ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች የመብት ጥሰትና አስተዳደር በደሎች ቁጥጥር ላይ ያልተፈጸሙ ስራዎች መኖራቸው ያነሱት አቶ አቡ በዚህም ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።  

በመሆኑም ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር ረገድም ያለበትን ክፍተት እንዲሞላም አመልክተዋል።   

የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ዋና እምባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ሪፖርቱን ሲያቀርቡ፤ በተቋሙ በሩብ ዓመቱ 903 አቤቱታዎችን ለመቀበል እቅድ ተይዞ 616 አቤቱታዎችን ተቀብሏል።

ከዚሁ ውስጥ 312 አቤቱታዎች በተቋሙ ለመታየት አግባብነት ያለው መሆኑን አንስተው ቀሪው ደረጃቸውን ያልጠበቁና ተቋሙ የማይመለከታቸው መሆናቸውን አንስተዋል።     

በተቋሙ ስር የማይወድቁ አቤቱታዎች ከግንዛቤ ማነስ ምክንያት በብዛት እንደሚመጡ ጠቁመው ችግሩን ለመፍታት የዜጎችን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

የዜጎችን እንግልት ለመቀነስም የጥሪ ማዕከል ለማቋቋም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።    

ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበርም ዌብ ፖርታል እየተዘጋጀ እንደሆነም ገልጸዋል።   

ተቋሙ አሰራሩን ለማዘመን የመረጃ ማዕከል ለማቋቋም የተለያዩ መሳሪያዎች ግዥ ፈፅሞ የሶፍትዌር ግዥ ጨረታ መውጣቱንም አክለዋል።          

የመረጃ ነጻነት አዋጁን በተመለከተም በ78 ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው የማድረግ ስራ ተከናውኗል ብለዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም