መቀሌ በመከላከያ ሠራዊቱ ቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ሠላም ሰፍኖባታል

104

መቀሌ፤ ህዳር 23/2013(ኢዜአ) መቀሌ ከተማ በመከላከያ ሠራዊቱ ቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ሠላም እንደሰፈነባት በስፍራው የተገኘው የጋዜጠኞች ቡድን ተመልክቷል።

በራያ ግንባር የነበረው የጋዜጠኞች ቡድን ከትናንት ጀምሮ በከተማዋ ቅኝት አድርጓል፡፡

የህወሓት ጁንታ ሲነዛው በቆየው ሽብር ሳቢያ የነዋሪዎቿ እንቅስቃሴ ውስንነት ቢታይበትም መቀሌ ፍፁም ሠላማዊ መሆኗን መመልከቱን የጋዜጠኞቹ ቡድን ገልጿል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት የመቀሌ ከተማን ከዘራፊው የህወሓት ቡድን በማስለቀቅ ሲቆጣጠራት ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱንም ታዝቧል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች የመከላከያ ሠራዊት ከገባ ጀምሮ ሠላም መሆኑን ማረጋገጣቸውን ቡድኑ በእማኝነት አስቀምጧል፡፡ 

'የመከላከያ ሠራዊቱ እናንተን ለመጨቆን ነው የሚመጣው፣ ከገባ ይገድላችኋል' እየተባለ ሲሰበክ የነበረው ፈጠራና ሀሰት መሆኑን አይተናል ብለዋል ነዋሪዎቹ፡፡

ነዋሪዎቹ የመከላከያ ሠራዊቱ በከተማዋ የተስፋፋውን የዘረፋ ወንጀል እንዲያስቆምላቸውም ጠይቀዋል፡፡ 

መንግሥት የተቋረጠውን የኤሌክትሪክና የቴሌኮም አገልግሎት ያስጀምርልን ሲሉም አመልክተዋል፡፡

በከተማዋ ሠላምና መረጋጋት ዙሪያ ከመከላከያ ሠራዊቱና ከመንግሥት ጋር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል ሲል የኢዜአ ሪፖርተር ከስፍራው ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም