በትግራይ ክልል በዘገባ ላይ የነበሩ ጋዜጠኞች ህዝቡ በሐሰተኛ መረጃ እንዳይደናገር ማድረጋቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል በዘገባ ላይ የነበሩ ጋዜጠኞች ህዝቡ በሐሰተኛ መረጃ እንዳይደናገር ማድረጋቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ ህዳር 23 /2013(ኢዜአ) በትግራይ ክልል በሚካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ለዘገባ የተሰማሩ ጋዜጠኞች ትክክለኛ መረጃ በማድረስ ህዝቡ በሃሰተኛ መረጃ እንዳይደናገር ማድረጋቸው ተገለጸ።
መንግስት በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻ ላይ በዘገባ ለተሳተፉ ጋዜጠኞች እውቅና ሰጥቷል።
በዕውቅና መርሐግብሩ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንን ጨምሮ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የአገር መከላከያ ሰራዊት ተወካዮች እንዲሁም የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አምባሳደር ሬድዋን በዚህ ወቅት እንዳሉት የመረጃ ፍሰቱ ሂደት ከባለድርሻ አካላት ጋር በየጊዜው ሲገመግም እንደነበር በማንሳት ወደ ግንባር የተሰማራው የሚዲያ ቡድን የመረጃ ክፍተትን በመሙላት ለህዝብ የአብርሆት ስራ ሲሰራ ነበር።
ትክክለኛ መረጃ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲደርስ በማድረግና ለሰራዊቱም ሞራል በመሆን የማይተካ ሚና እንደነበራቸው ነው የጠቀሱት።
ጋዜጠኞች ከሰራዊቱ እኩል በመንቀሳቀስ የሰራዊቱን ጀብድና በየስፍራው ያለውን የህዝብ ስሜት በትክክል ማሳየት ችለዋል ብለዋል።
ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለ ህግ ማስከበር ሂደት ገለጻ ለማድረግ የመረጃ ግብዓት ሲያቀርቡ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ለአገረ መንግስት ግንባታ፣ ህዝባዊ አብሮነት ድልድይ ለመሆን ጋዜጠኞች በተሰማሩበት መስክ የተጫወቱት ሚና ከፍ ያለ እንደነበርም ነው የተገለጸው።
የመከላከያ ሰራዊት የሚዲያ ስራዎች ዳይሬክተር ብርጋዴል ጀኔራል ኩማ ሚዴቅሳ ለ30 ዓመታት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲሰራ በነበረው የህወሃት ጁንታ ጥቃት ተከትሎ የህግ ማስከበር ዘመቻው ድንገተኛ ነበር ብለዋል።
በጦር ዘገባ ዙሪያ የአዘጋግብ ስልጠና ሳይሰጣቸው የተሰማሩ ጋዜጠኞች በአገር ፍቅር ወኔ በመስራት የወታደሩን ሞራልና ስነ ልቦና የሚደግፍ ስራ እንደሰሩም ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው በህግ ማስከበሩ ሂደት የተገኘው ድል ሁሉም በተሰማራበት መስክ ባከናወነው ውጤታማ ስራ የተገኘ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ ሚዲያውም "ለህዝብ መረጃ በማድረስና የሀሰት ጥይቶችን በመከላከል" እንደ ሰራዊቱ ሁሉ ሚናቸው ጉልህ ነበር ብለዋል።
በተልዕኮው የሚዲያው ትብብር የታየበት፣ ህዝቡም ሰራዊቱን እንዲደግፍ የሚያስችሉ ውጤታማ ስራዎች የተከናወኑበት እንደነበር አንስተው፤ ጋዜጠኞች በህግ ማስከበር ዘመቻው "የዐይን ምስክሮች፣ ለዛሬ የዜና ለነገ ደግሞ የታሪክ ነጋሪዎች ናቸው" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ፤ በወቅታዊ ሁኔታ ጋዜጠኞች ወደ ግንባር ተሰማርተው በሰሩት ስራ ህዝቡ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ አስችሏል ብለዋል።
ጋዜጠኞቹ በህግ ማስከበሩ ዙሪያ ስልጠና እንኳን ሳይሰጣቸው ብስለት ባለው አዘጋገብ በሰሩት ስራም ዶክተር ጌታቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ለጋዜጠኞች እንዲበረታቱ የተሰጠው እውቅና ተገቢ መሆኑን ገልጸው አዘጋጁን አካል አመስግነዋል።