ቀጥታ፡

ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የክልሉ ህዝብ በጥንካሬ ሊሰራ ይገባል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ፣ ህዳር 23/ 2013(ኢዜአ) የክልሉ ነዋሪ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የክልሉን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በጋራ ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።

’’እኩልነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለጋራ ብልጽግና ’’ በሚል መሪ ሀሳብ 15ኛው የኢትየጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በክልል ደረጃ በጎግ ወረዳ ፑኝውዶ ከተማ ተከብሯል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በክብር በዓሉ ወቅት፤ ጁንታው ህወሓት ባለፉት ዓመታት ልዩነቶችን የሚፈጥሩ ከፋፋይ ትርክቶችን በመስበክ የኢትዮጵያ ህዝቦችን አንድነትና ወንድማማችነት በመሸርሸር ሀገርን ለመበተን ያሰበው ዓላማ ከንቱ ሆኖ ቀርቷል ብለዋል።

ህዝቡ አንድነቱንና አብሮነቱን በማጎልበት የክልሉን ብሎም የሀገርን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

ከሃዲው ጁንታ ጋምቤላን ጨምሮ ታዳጊ የሚባሉ ክልሎችን በሞግዚትነት በመያዝ በሀገራቸው ጉዳዮች ላይ እኩል የመወሰን መብታቸውን በመንፈግ የተለያየ ጭቆናና ግፍ ሲፈጽም መቆየቱን አስታውሰዋል።

በተለይም በጋምቤላ ክልሉ ያለውን ሰፊ መሬት በመቀራመትና ለባንክ ማስያዝ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የዘረፈ ጸረ ህዝብ ቡድን መሆኑን አስረድተዋል።

የጥፋት ቡድኑ ከአሁን በፊት በኢትዮጰያ ህዝቦች ላይ ሲፈጽማቸው የነበሩት ግፍና በደሎች አልበቃው ብሎት በሀገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች ንጹሃን ላይ አረመኔያዊ የክህደት ድርጊት መፈጸሙን ገልጸዋል።

ይሁን አንጂ በሠራዊቱ ቆራጥ ተጋድሎ አከርካሪው ተመቷል ብለዋል።

እያንዳንዱ የከሃዲው አባላት ተይዘው ለህግ እስኪቀርቡ ድረስና ቀደም ሲል በዘረጉት የጥፋት ሴራ የጸጥታ ችግር እንዳይከሰት ሁሉም ዜጋ የአካባቢውን ሰላም ነቀቶ እንዲጠበቅ ርዕሰ መስተዳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በክብር በዓሉ የተሳተፉት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የህወሓት ቡድን ባለፉት ዓመታት ህገ መንግስቱን በተግባር ሳይሆን በቃል እየዘመረ የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች መብት የነፈገና የሀገርን ሀብት የዘረፈ ቡድን ነው ብለዋል።

ቡድኑ ባለፉት ዓመታት በፈጸማቸው አፈናና የሀብት ዘረፋ የኢትዮጵያ ህዝቦች በድህነት ቀንበር ውስጥ እንዲወድቁ ማድረጉንም አውስተዋል።

አሁን ያለውን ሀገራዊ ለውጥ ወደ ፊት በማሻገር ከድህነት ለመላቀቅ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን በማጠናከር በጋራ ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።

በተለይ በጋምቤላ ክልል ያለው ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ጭምር የሚበቃ በመሆኑ ወደ ልማት በመለወጥ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማደረግ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።

ከሲዳማ ክልል በመምጣት በዓሉ ከጋምቤላ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር የማክበር እድል በማግኘታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ አቶ ጁል ናንጋል በበኩላቸው የዘንደሮው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል የተከበረው ጥላቻና ጥርጣሬን በማስወገድ ህዝቡ በአንድነትና ፍቅር ሀገርን ከጁንታው መታደግ በተቻለበት ወቅት በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በጋምቤላ ክልል ደረጃ በደም ልገሳ፣ በፓናል ውይይትና ሌሎች ዝግጅቶች ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም