ቀጥታ፡

የመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ በምዕራብ ግንባር በዓይን ምስክሮቹ ጋዜጠኞች አንደበት

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23/2013 (ኢዜአ) የአገር መከላከያ ሠራዊት የሕግና የአገር ሕልውና የማስከበር ተልዕኮ በዓይን ምስክሮቹ ጋዜጠኞች አንደበት

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሸት የአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ በህወሓት ከሃዲ ቡድን የተፈጸመበትን ጥቃት ተከትሎ መንግስት በወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ መቀሌን ተቆጣጥሯል።

የሠራዊቱን የሕግ ማስከበር ተልዕኮ ከዳንሻ እስከ አድዋ ባሉ የጠር ሜዳ ውሎዎች በመገኘት የዘገባ ስራዎቹን ለመስራት ዕድሉን ያገኙ የሚዲያ ባለሙያዎች ትናንት ምሽት በመንግስት እውቅና ተችሯቸዋል።

ጋዜጠኞቹ ለጠላት እጅ ላለመስጠት ለቀናት በጀግንነት የተዋጉትን የ5ኛ ሜካናይዝድ ዋና አዛዥ ጄኔራል ሙሉዓለም አድማሱን በማነጋገር ስራቸውን ስለመጀመራቸው ይተርካሉ።

በሣምንታት የጦር ሜዳ ዘጋቢነት ቆይታቸውም ከመሄዳቸው በፊት ካሰቡት በተለየ በሠራዊቱ ጀግንነት፣ መተሳሰብና ሕዝባዊነት ተማርከው ለመመለስ ማቅማማታቸውን ሁሉም የሚጋሩት እውነት ነው።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋዜጠኛ ዳዊት መስፍን በግዳጅ ቀጣና ለዘገባ በተሰማራበት አጋጣሚ በሰማቸውና በገጠመኞቹ ከሠራዊቱ 'ለሕይወት መርህ የሚሆኑ ቁምነገሮች’ን እንደገበየ ይተርካል። 

ወታደሩ አገር ከነፍሱ በላይ እንደሆነ፤ ሞቶ አገር ለማዳን እንደሚሰራ በተለያዩ ገጠመኞቹ በተግባር ማረጋገጡን ይናገራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኛ እንዳሻው ሹሜ በበኩሉ ወታደር ከየትኛውም ሙያ በተለየ በስራ ደክሞ ሳያርፍ ለአገሩ እንደሚሰዋ በተግባር ያረጋገጠበት ዕድል ማግኘቱን ይገልጻል። 

ጄኔራል ባጫ ደበሌ "ሰው ሰርቶ ያርፋል፤ ወታደር ደክሞ ይሞታል” የሚሉትን ንግግር በተግባር ያየበት አጋጣሚ እንደሆነም ገልጿል።

እነዚህ ጋዜጠኞች በጦር ግንባር ቆይታቸው ዕውነት እንደምታሸንፍ ያዩበት፣ ከሠራዊቱ ጋር በፍቅርና በመረዳዳት የቆዩበት፣ በስራቸውም ለሕዝብ ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ ሀሰትን የተዋጉበት የሕይወታቸው አጋጣሚ እንደሆነ ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ ዮሐንስ ፍስሃ በሠራዊቱ ላይ የተፈጸመው ድርጊት ውስጥን የሚነካ በመሆኑ የጋዜጠኞቹም ቡድን በእልህና ቁጭት ስራቸውን በትብብር ለመስራት እንዳነሳሳቸው ይገልጻል።

በቆይታቸው ኢትዮጵያዊትን፣ አገርን መውደድን፣ የሠራዊቱን ጀግንነትና መተሳሰብ፣ የሕዝብ አለኝታነት የተመለከተበት እንደነበረ ነው የተናገረው።

በተመሳሳይ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ የካሜራ ባለሙያው ጅብሪል ጉደታም ወደ ዘመቻው ሲሰማራ ፍራቻ ቢያድርበትም ሠራዊቱን ከተቀላቀለ በኋላ ግን የእነሱ ፍቅርና መረዳዳት አስደንቆት ለመመለስ ማቅማማቱን ይናገራል።

የግንባሩ የሚዲያ ስራዎች አስተባባሪ ኮሎኔል አባተ ንጋቱ የጋዜጠኞቹ ወኔ በቤተሰባዊነትና በአንድ አይነት ስነ-ልቦና ከወታደሩ ጋር ተንቀሳቅሶ የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል የሚሻ እንደነበር መስክረዋል።

ይህ እንዲሆን ያደረገው የሠራዊቱ መገፋትና በከሃዲዎች የተፈፀመበት ከባድ ግፍ እንደነበር ገልጸው፤ የጋዜጠኞቹ ወደ ስፍራው መሰማራት ሠራዊቱ አገር ከጥቃት እንድትድን በትጋት እንዲዋጋ፣ በሰሩት ስራም የሠራዊቱ ሞራል እንዲገነባ ስንቅ ሆኗል ብለዋል።

ከሃዲው የህወሓት ቡድን ሠራዊቱ በተቆጣጠራቸው ከተሞች ሳይቀር የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ሲያሰራጭ ሚዲያው ሀሰተኛውን መረጃ በማጋለጥና የሕዝቡን ተባባሪነት በማሳየት አደናጋሪ መረጃዎችን በማጥራት ውጤታማ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ከዚህም በላይ ጋዜጠኞቹ ከዳንሻ አድዋ ደርሶ የዘገባ ስራዎችን አከናውኖ ለመመለስ ሳይሆን ከሠራዊቱ ጋር ለመቀጠል በመፈለግ ከግንባር መልስ ወቅት ቅሬታ እንደነበረ ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም