የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 23/2013 ዓ.ም (ኢዜአ) ዘንድሮ የሚከበረው 15ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ካለፉት ዓመታት በተለየ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን የበለጠ በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።
ኢትዮጵያዊያን በጋራ እሴቶቻቸው ላይ የተሻለ ግንዛቤ ይዘው ኅብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን በሚያጠናክሩበት መልኩ ሕገ-መንግስቱ የፀደቀበት ቀን ሕዳር 29 እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።
"ኢትዮጵያን በአንድ መድረክ እንያት" በሚል መሪ ሃሳብ ኤግዚቢሽን ነገ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ይከፈታል።
በ1987 ዓ.ም የጸደቀውን የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት በየዓመቱ ለመዘከር የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሚል መከበር ከጀመረ 14 ዓመታት ሆኖታል።
የበዓሉ መከበር ዓላማ ዜጎች ሕገ መንግስቱንና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በአግባቡ ተረድተው ለተግባራዊነቱ የድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግና በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ አንድነትን ማጠናከር ነው።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ “ባለፉት ዓመታት በተከበሩ በዓላት ብሔር ብሔረሰቦችን በማቀራረብና ባሕላቸውን ቢያስተዋውቅም የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሕገ መንግስቱና በፌዴራል ስርዓቱ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲይዙ አልተደረገም” ብለዋል።
እንደ አፈ ጉባዔው ገለጻ፤ የዘንድሮው 15ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ካለፉት ዓመታት በተለየ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን የበለጠ በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል።
በዓሉ የፌዴራል ስርዓቱ በአግባቡ እንዳይተገበር ሲያደርግ በነበረው የህወሓት ቡድን ላይ ሕጋዊ እርምጃ በተወሰደ ማግስት መከበሩ ድርብ በዓል እንደሚያደርገው ነው አቶ አደም የገለጹት።
ሕገ መንግስቱ በግልጽ ያስቀመጣቸው የግለሰቦችና የቡድኖች መብቶች በጽንፈኛው ቡድን ምክንያት ሲጣሱ እንደነበረም አንስተዋል።
መንግስት ባለፉት ሁለት ዓመታት ትክክለኛ የፌዴራልዝም ስርዓት ለመተግበር ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ “ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ስለ ሕገ መንግስቱና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ይሰራል” ብለዋል።
በዓሉ የእኩልነትና የኅብረ ብሄራዊ አንድነት ችቦ የሚለኮስበት፣ በደም ልገሳ የመከላከያ ሠራዊቱ የሚበረታታበት፣ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የፓናል ውይይቶች የሚካሄዱበት እንደሚሆን ተገልጿል።
15ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "እኩልነትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለጋራ ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ይከበራል።