ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅናትና ታጋሽነት ትምህርት መውሰዳቸውን በሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅናትና ታጋሽነት ትምህርት መውሰዳቸውን በሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ
ሀዋሳ፣ ህዳር 23/2013( ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለውጡን በመምራት ሂደት ውስጥ ከጁንታው ያጋጠማቸውን ፈተና ለማለፍ ካሳዩት ፅናትና ታጋሽነት ትምህርት መውሰዳቸውን በሀዋሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
ነዋሪዎቹ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሰጡትን ማብራሪያ በመገናኛ ብዙሃን ተከታትለዋል።
በዚህም ሀገሪቱን ሲመሩ በቆዩባቸው ጊዜያት ይገጥሟቸው የነበሩ ፈተናዎችን ለህዝቡ ይፋ ማድረጋቸው ኢትዮጵያውያን የለውጡ ሂደት ግልጽ እንዲሆንላቸው ማስቻሉን ተናገረዋል፡፡
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ መላኩ አቡ በሰጡት አስተያየት የጁንታው አባላት ከለውጡ በፊትም ሆነ በኋላ በሀገሪቱና ህዝቦቿ ላይ ሲያደርሱ የነበሩት ግፍ በአሸባሪነት ሊያስፈርጃቸው የሚገባ ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ህይወታቸውን አደጋ ውስጥ ጥለው በከባድ ፈተና ውስጥ ሀገሪቱን እየመሩ እንደነበር መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ላይ የነበራቸውን የተዛባ አመለካከት ከማብራሪያቸው በመገንዘብ አሁን ማስተካከል መቻላቸውንና ይህን ፈተና በብስለት ለማለፍ ካሳዩት ፅናትና ታጋሽነት ትምህርት መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡
ወጣት ፍቅሩ ፍሬሁን በበኩሉ ከዚህ በፊት እንደሌሎች ሰዎች እኔም በጥፋት ኃይሎች ላይ ለምን አፋጣኝ እርምጃ አይወሰድም የሚል አቋም ነበረኝ ብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ኃይሎች ለምን በትእግስት ሲያልፏቸው እንደነበር አሁን ላይ በቂ ግንዛቤ ማግኘቱንና ከሳቸው የትዕግስት ጉዞ መማሩን ገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጡን ሂደት እልህ አስጨራሽ በሆነ ትግል መምራታቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ መስፍን አብነው ናቸው፡፡
ዶክተር አብይ የተጓዙበት የጥበብ መንገድ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆናቸውን ያስመሰከረ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይ ለሚጠብቀን የለውጥ ጉዞ ሁላችንም ከመንግስት ጎን በመቆም ሀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል፡፡