ቀጥታ፡

የአብሮነት እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ወደ ፊት ማራመድ ይገባል...አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

ህዳር 23/2013 (ኢዜአ) የቆየውን የአብሮነትና የአንድነት እሴቶች ይበልጥ በማጠናከር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ወደ ፊት ማራመድ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ተናገሩ።

የህብረ ብሄራዊ አንድነት ችቦ ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ጋምቤላ ክልል ሲገባ አቀባበል ተደረገለት።

ርዕሰ መስተዳድሩ በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ የህወሃት ጁንታ ሲያራምደው የነበረውን የከፋፋይ አስተሳሰብ በማስወገድ አንድነትንና አብሮነትን የመገንባቱ ተግባር ሊጠናከር ይገባል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነታቸውንና አብሮነታቸውን በማጠናከር የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥና የብልጽግና ጉዞ ወደ ፊት ማራመድ እንዳለለባቸውም ተናግረዋል።

የህብረ ብሄራዊ አንድነት ችቦ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በቅብብሎሽ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል እንዲከበር የተወሰነው በህዝቦች መካከል ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን አንድነትና ወንድማማችነት ለማጠናከር መሆኑን አቶ ኡሞድ አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ ወይዘሮ ዘርፈሸዋል ንጉሴ የህብረ ብሔራዊ አንድነት ችቦውን ለጋምቤላ ክልል ሲያስረክቡ "ኢትዮጵያ ለሁሉም የምትበቃ ቤታችን ፣ከለላ እናታችን ናት'' ብለዋል።

በሀገሪቱ ሰላም፣እድገትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአንድነትና በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ጁንታው ሀገር ለማፍረስ የከፈተው ዘመቻ በተቀለበሰበት ማግስት እየተከበረ መሆኑ የተለየ እንደሚያደረግው ጠቅሰዋል።

የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ -ጉባኤ አቶ ጁል ናጋል በበኩላቸው ባለፉት 27 ዓመታት ህዝቦችን ለመለያየት ሲሰበክ የነበረውን ከፋፋይ አስተሳሰብ በማስወገድና አንድነትን በማጠናከር የተጀመረው ልማት ለማስቀጠል በጋራ መረባረብ ይገባል ብለዋል።

በሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ጭምር ታጅቦ ትናንት ጋምቤላ ከተማ የደረሰው የህብር ብሄራዊ አንድነት ችቦ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች አቀባበል ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም