ህወሃት ሀገር ለማፍረስ የፈፀመው ተግባር በሽብርተኝነት እንደሚያስፈርጀው የህግ ምሁራን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ህወሃት ሀገር ለማፍረስ የፈፀመው ተግባር በሽብርተኝነት እንደሚያስፈርጀው የህግ ምሁራን ገለጹ
አዳማ፣ ህዳር 23 /2013(ኢዜአ) ህወሃት ሀገር ለማፍረስ ህዝቦችን እያጋጨ በማጋደል ሲፈጽማቸው በነበሩት ወንጀሎች በሽብርተኝነት እንደሚያስፈርጀው በኦሮሚያ የፍትህ አካላት ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ኢንስቲትዩት የህግ ምሁራን ገለጹ።
ምሁራኑ ለኢዜአ እንደተናገሩት ጁንታው በሀገር ላይ የፈፀመው የክህደት ተግባር የወንጀል የመጨረሻው ቅጣት የሚያሰጥ ነው።
በኢንስቲትዩቱ የህግ ምሁር አቶ ሻምበል ሆርዶፋ በሰጡት አስተያየት ቡድኑ ባለፉት ዓመታት ሀገር ለማፍረስ ህዝቦችን በየቦታው ሲያጋጭ ፣ ሲያገዳድልና ሲያሸብር የነበረ ነው ብለዋል።
ሀገር ለማፍረስ በመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ከመፈፀሙም ባለፈ የሀገር መሰረተ ልማቶችን ማውደሙን አውስተዋል።
የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ የራሱን ቴሌቭዥኖችና ማህበራዊ ገፆችን በመጠቀም ብሔር ብሔረሰቦችን ለአመፅ ሲቀሰቅስ እንደነበር ተናግረዋል።
ራሱ በከፈተው ጦርነት ጎረቤት ሀገር ጭምር ስም በማጠልሸት የትግራይ ህዝብ በስጋት እንዲኖርና ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲነጠል በማድረግ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ያወከ የሽብር ተግባር መፈፀሙንም አቶ ሻምበል ገልጸዋል።
ህወሃት በአገዛዝ ዘመኑ የመከላከያ ሠራዊቱ በአንድ አካባቢ ሰዎች ብቻ እንዲያዝ ማድረጉ በራሱ ወንጀል ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ወታደራዊ መኮንኖችን የራሱ የጥፋት ዓላማ እንዲያሳኩለት ማስኮብለሉ የሀገር ክህደት መሆኑን ተናግረዋል።
ቡድኑ የፈፀማቸው ተደራራቢና አጸያፊ ወንጀሎች በወታደራዊና የሀገር ክህደት ወንጀል በሽብርተኝነት የሚያስጠይቀው በመሆኑ ለፍርድ መቅረብ አለበት ብለዋል።
ከቡድኑ ጋር ግንኙነት በመፍጠር ሀገር የማፍረስ ጥፋት የሰሩ፣ በሀገር ውስጥና ውጭ ሆነው ህዝብን ከህዝብ ጋር የሚያጋጩና ለጥፋት የሚቀሰቅሱ ግለሰቦችና ቡድኖች ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ጁንታው ህግ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ ተግባር መፈፀሙን የገለጹት ደግሞ በኢንስቲትዩቱ የህግ መምህርና ተመራማሪ ወይዘሮ አዱኛ አህመድ ናቸው።
የሀገር መከላከያ ላይ የፈጸመው የጥቃት ወንጀሉ እስከ ሞት የሚያስቀጣ ከመሆኑም ባለፈ ቡድኑን በሽብርተኝነት የሚያስፈርጅ ነው ብለዋል።
ህወሃት የፌዴራል መንግስት ህልውና ጥያቄ ውስጥ የከተተ፣ የህግ አውጭ አካላትን ጭምር ውሳኔ ወደ ጎን በመተው ምርጫ ማካሄድና ህግ መንግስታዊ ስርዓቱ መቃረኑ ከባድ ወንጀል መሆኑን ገልጸዋል።
የህግ የበላይነት ማስከበር የመኖርና ያለመኖር ህልውና በመሆኑ ህጉን ጥሰው የተገኙ ቡድኖችና ግለሰቦች ለህግ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት ማግኘት እንዳለባቸውም ወይዘሮ አዱኛ ተናግረዋል።
ትግራይ ክልል መቀሌ ድረስ የሰላም አምባሳደር ሆነው እናቶችን ወክለው መሄዳቸውን የገለጹት የህግ ምሁሩዋ፣ በወቅቱ የትግራይ ክልል መሪዎች ''በክልላችን ሰላም አለ፣ ምን ልትሰሩ ነው የመጣችሁት፣ ሰላም ወደ ሌለበት ክልሎች አትሄዱም እንዴ? ብሎን ተሳልቀውብናል'' በማለት አውስተዋል።
''ተንበርክከን ለሰላም ስንል አመራሮቹን ተማፅነን ነበር፤ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ስለ ሀገር ሰላምና አንድነት መጠበቅ ሲለምኗቸው እንደነበር እኔ ራሴ በተግባር አይቻለው'' ሲሉም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንግስት ጎን በመቆም ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በትጋት እንዲሰራም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።