የህወሓት ጁንታ በፈፀመው ክህደት አዝነናል--- በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች - ኢዜአ አማርኛ
የህወሓት ጁንታ በፈፀመው ክህደት አዝነናል--- በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች
አዲስ አበባ ህዳር 22/2013 (ኢዜአ) የህወሓት ጁንታ በአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ በፈፀመው ጥቃትና የአገር ክህደት ማዘናቸውን በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች ገለጹ።
መንግስት ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ የጀመረውን ተግባር በፍጥነት ሊፈጽም ይገባልም ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
በመድረኩም የክልሉ ተወላጆች የህወሓት የጥፋት ቡድን በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ያደረሰው ጥቃት ታሪክ የማይረሳውና "የትግራይ ተወላጆችን አንገት ያስደፋ" መሆኑን ነው የገለጹት።
በውይይቱ ላይ ከተሳተፉት ማካከል አቶ ማስረሻ ፍሰሃ እንዳሉት የትግራይ ህዝብ በጨዋነቱ፣ ለእውነት በመቆምና እና በአገር ወዳድነቱ ይታወቃል።
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ታሪክን የሚያጠለሹ ባንዳዎች በፈጸሙት የክህደት ተግበር ብዙዎቻችን አዝነናል ብለዋል።
"የትግራይ ህዝብ ንጹህ ውሃ እንኳ ሳያገኝ ለዘመናት በችግር ውስጥ ሆኖ ችግሩ ሳያንሰው ህዝቡን ለጦርነት ተነስ ማለት ፣ መሰረተ ልማት ማፍረስ የአውሬነት ባህሪ ነው'' ሲሉ የተናገሩት ደግሞ አቶ ኃይሌ ገብረሚካኤል የተባሉ የከፍለ ከተማው ነዋሪ ናቸው።
የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን የክህደት ተግባር አሳፋሪ መሆኑን ገልጸው፣ መንግስት እያደረገ ያለውን ህግ የማስከበር ተግባር በማጠናከር ወንጀለኛ ቡድኑን በፍጥነት ለህግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።
የቡድኑ አሳፋሪ ተግባር እጂጉን ያስቆጣቸው ወይዘሮ ፀሐይ ተክለስላሴ ደግሞ ድርጊቱ የእናትን ጡት መንከስ ነው'' ብለዋል።
መምህር አጸደ ካሃሳይ በበኩላቸው በካሃዲዎች እኩይ ተግባር አዝነናል፤ የትግራዋይን ታሪክ ለማበላሸት የፈጸሙት ሴራ እና ክደት ታሪክ የማይረሳው ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ብሔር ብሄረሰቦች ጋር የተዋለደ ህዝብ መሆኑን በማንሳት አጥፊዎቹ ሊጠየቁ እንደሚገባና የትግራይ ህዝብ ሰላም ፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ተሳታፊዎቹ በክልሉ ተቋርጠው የነበሩት የኤሌክትሪክ ኃይል እና የቴሌኮሙንኬሽን አገልግሎቶች እንዲመለሱ ጠይቀዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚደቅሳ ከበደ፤ መንግስት በጉዳዩ ለይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
"በቀጣይም የትግራይ ህዝብ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ከልማቱ እና ከሰላሙ በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚሆንበት ጠንካራ ሥራ ይሰራል" ብለዋል።