የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የውጭ ባለሃብቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታተ የሚያስችል ስትራቴጂ እያዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የውጭ ባለሃብቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታተ የሚያስችል ስትራቴጂ እያዘጋጀ ነው
አዲስ አበባ ህዳር 22/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ኢንቨስት የሚያደርጉ የውጭ ኩባንያዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታተ የሚያስችል ስትራቴጂ እያዘጋጀ መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ የተሻሻለውን የኢንቨስትመንት አዋጅ አስመልክቶ ዛሬ ገለጻ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ እንደተናገሩት፤ የተሻሻለው የኢንቨስትመንት አዋጅ በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ ነው።
ከዚህ ቀደም ለውጭ ኩባንያዎች ዝግ የነበሩት የኢንቨስትመንት ዘርፎች ጭምር ክፍት ከማድረጉ በላይ "በተለይ የውጭ ባለሃብቶች በቀላሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ያግዛል" ብለዋል።
በኢንቨስትመንት ዘርፍ ግልጽነት በመፍጠር በዘርፉ የሚነሱትን አለመግባባቶች በቀላሉ ለመፍታት አስተዋጽዖ እንዳለውም ነው ኮሚሽነሯ የገለጹት።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ የውጭ ባለሃብቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ስትራቴጂ ኮሚሽኑ እያዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም ኮሚሽኑ የውጭ ባለሃብቶች መዋለንዋያቸውን ሲያፈሱ የሚያጋጥማቸውን የተለያዩ ውስጣዊ ችግሮች ለመፍታት በቅርበት እንደሚሰራና እንደሚደግፍ ተናግረዋል።
ባላሃብቶቹ ላይ ኮቪድ-19 ካደረሰው ተጽዕኖ ጀምሮ ሌሎች ያሉባቸውን ችግሮች ለማቃለል ኮሚሽኑ የሚቻለውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ኮሚሽነሯ አረጋግጠዋል።
አዲሱ የተሻሻለው የኢንቨስትመንት አዋጅ መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም መውጣቱ ይታወሳል።
አዋጁ ተሻሽሎ እንዲወጣ የተደረገው የአገራዊ ኢኮኖሚውን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ለማፋጥን፣ የወጪ ንግድን ለማስፋፋት እና ሠፊና ጥራት ያለው የሥራ ዕድል ለመፍጠር በማሰብ ነው።
ወደ አገር ውስጥ የሚመጣውን የውጭ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንት መጠንና የተሳትፎ መስክ በማስፋት የዕውቀት፣ የክህሎት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ሥርጸትን ለማፋጠንም ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ጎን ለጎንም በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል ዘላቂ እና ተመጋጋቢ ትስስርን የሚያሳልጥ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመዘርጋትም በማስፈለጉ ጭምር አዋጁ መውጣቱ ታውቋል።