ቀጥታ፡

አብሮነታችንን በማጠናከር ለሰላምና ልማት የበኩላችንን ሚና መወጣት አለብን- ትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ

አዲስ አበባ ህዳር 22/2013 (ኢዜአ) "አብሮነታችንን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት የበኩላችንን ሚና መወጣት አለብን" ሲሉ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ጥሪ አቀረቡ።

ሚንስትሯ ይህን ያሉት የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሰራተኞች 15ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ዛሬ ባከበሩበት ወቅት ነው።

እለቱም "ህብረ ብሔራዊነት መገለጫችን አንድነት ህልውናችን፤ እኩልነትና ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ለጋራ ብልጽግናችን" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተከበረው ።

ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ  በዚህን ወቅት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን አብሮነት በማጠናከር ለዘላቂ ሰላምና ልማት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተቀናጀ ጉልበት የጋራ ፈተና የሆነውን ድህነት ማሸነፍ አለባቸው ሲሉም ነው የተናገሩት።

በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ሰላምን፤አንድነትና ልማትን ለማረጋገጥ የተጠናከረ ስራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በዘርፉ በተዘጋጀው የ10 ዓመት መሪ እቅድ አማካኝነት የትራንስፖርት ተደራሽነትን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግም ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

የበዓሉ ታዳሚ ወይዘሮ ዝናሽ ማቲዎስ በበኩላቸው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበሩ ኢትዮጵያዊያን እርስ በርስ እንዲተዋወቁ ከማድረጉም በላይ ለሰላም ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም አብሮነታችንን ይበልጥ ማጠናከር አለብን ብለዋል።

መንግስት ኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ትስስር በቀጣይነት የሚያጎለብቱ የተለያዩ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም