ቀጥታ፡

ለሀገራዊ አንድነት መጠናከር ሁሉም እንዲነሳሳ ጥሪ ቀረበ

ሀዋሳ ህዳር 22 / 2013 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል የሚገኙ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር በመነሳሳት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ። 

በሲዳማ ክልል ደረጃ 15ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ዛሬ  በሀዋሳ ከተማ  ሲከበር የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ ሰለሞን ላሌ እንደተናገሩት የሲዳማ ህዝብ ሲታገልለት የነበረው የአደረጃጀት ጥያቄ  በለውጡ አመራር  ምላሽ አግኝቶ እውን በመሆኑ የዘንድሮ በዓል  ከወትሮው በተለየ ያከበረዋል።

ሌላው በዓሉን ለየት የሚያድርገው  ጉዳይ በትግራይ ክልል ሲካሄድ የነበረው ህግ የማስከበር ዘመቻ በስኬት በተጠናቀቀ ማግስት  የሚከበር መሆኑ እንደሆነ አመላክተዋል።

የዘንድሮው በዓል አከባበር በሀገራችን ሰላም ላይ የሚያጠነጥን ሆኖ ችግሮቻችንን በውይይት የመፍታት አቅማችንን የምናጎለብትበት፣የህገመንግስቱን መርሆዎችና እሴቶችን አጉልተን የምንመለከትበት ነው ብለዋል።

በሲዳማ ክልል የሚገኙ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ሃገራዊ አንድነትና የብልጽግና ጉዞን  ለማጠናከር በመነሳሳት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በዓሉ ኮሮናን ለመከላከል  ታሳቢ ባደረገ መልኩ ከህዳር 17 እስከ 25/2013 ዓ.ም. በተለያዩ ኩነቶች በክልሉ እንዲከበር በተወሰነው መሰረት በ36  ወረዳዎችና  ከተማ አስተዳደሮች መከናወኑን አመልክተዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ተሰማ ዲማ በበኩላቸው  በዓሉን ስናከበር እስከ ዛሬ የነበሩ ችግሮቻችንና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን እየተገዳደሩ ያሉ ተግባራትን በቁርጠኝነት ለማስወገድ መነሳታችንን በተግባር ማሳየት ይኖርበናል ብለዋል።

ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት ተሰባስበው በዓሉን ስላከበሩ አንድነት አይመጣል ያሉት አማካሪው ይልቁንስ ለግጭት ሲዳርጉ የነበረውን ልዩነት በመተው  ሀገሪቱን ወደ ፊት ለማሻገር በጋራ መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ወጣት ምህረት ገነነ በሰጠችው አሰተያየት  በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች  ከጫፍ እስከ ጫፍ ተገናኝተው አንዱ ስለሌላው የሚያውቅበት መድረክ በመሆኑ በደስታ እንደምታከብረው ገልጻለች።

እኛ ወጣቶች የኢትዮጵያን አንድነት ከሚሸረሽር ተግባርና አመለካከት በመራቅ ለሀገር እድገትና ብልጽግና ልንረባረብ ይገባል ብላለች።

በዓሉ በሀዋሳ ከተማ በፓናል ውይይት ሲከበር  ትኩረት ያደረገው  የህወሀት ኢ - ህገመንግስታዊ እንቅስቃሴ እና ፌዴራል ስርዓቱን ለማዳን የተደረጉ ጥረቶች ፣ የወጣቶች ሠላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ትግል ለህብረ ብሄራዊ አንድነት ላይ ነው።

በፓናል ውይይቱ ከክልሉ ማዕከል ፣ዞን እና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ አመራሮች ፣የመንግስት ሠራተኞች ፣የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች  ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም