ለትግራይ ክልል ሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንደሚሆን ትዴፓ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ለትግራይ ክልል ሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንደሚሆን ትዴፓ ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 22/2012(ኢዜአ) ለትግራይ ክልል የሰላምና የዴሞክራሲ ግንባታ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንደሚሆን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ንግግራቸው ያስቀመጡትን አቅጣጫ ተግባራዊ እንዲያደርግም ጠይቋል።
የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የህወሃት የጥፋት ቡድን አመራር በትግራይ ህዝብ ላይ ያደረሰው ግፍና ጭቆና ተዘርዝሮ አያልቅም በማለትም ገልጸዋል።
"ቡድኑ ከትግራይ ህዝብ ባለፈ በመላ ኢትዮጵያ የፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ፀረ-ህዝብና ፀረ- አገር አጀንዳ እንደነበረው ማሳያ ነው" ይላሉ።
የመከላከያ ሰራዊት የትግራይ ህዝብ ጉዳት እንዳይደርስበት ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ክልሉን ከጁንታው ነጻ ማውጣቱ የሚደነቅ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
"ለረጅም ጊዜ በአፈናና በበደል የቆየው ክልል ነጻ በመውጣቱ ፓርቲው ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶታል፤ ፀረ-ህዝብ የሆነውን ስርዓት እስከመጨረሻው ለመቅበር ቁርጠኛ ነን" ብለዋል ዶክተር አረጋዊ።
ከዚህ በኋላ ለትግራይ የሚያስፈልገው ህዝቡ የሚቆጣጠረው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ይህን ለማድረግ ፓርቲያቸው ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ሃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን ለጦርነት የሚማግዱበት ጊዜ ማብቃቱን የገለጹት ሊቀመንበሩ፤ ህዝቡን በስነ- ልቦናም ሆነ በኢኮኖሚ መልሶ በማቋቋም ረገድ የኢትዮጵያ ህዝብ ትብብር ወሳኝ መሆኑንም አስታውቀዋል።
''በትግራይ ክልልም ሆነ በመላው ኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማምጣት እያንዳንዳችን ድርሻ አለን'' ያሉት ዶክተር አረጋዊ፤ በቡድኑ የወደሙ መሰረተ ልማቶች በአጭር ጊዜ መልሰው እንደሚገነቡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለ በመሆኑ''ትግራይን መልሶ በመገንባት በኩል እያንዳንዱ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት አለበት'' ብለዋል።
በትግራይ ክልል ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድና ለህዝቡ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት ፓርቲያቸው ድጋፍ እንደሚያደርግም ዶክተር አረጋዊ አረጋግጠዋል።
እንደ ዶክተር አረጋዊ ገለጻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት ያደረጉት ንግግር ያለፈውን፣ የወደፊቱንና የቀጣዩን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ የተነተነ፣ አርቆ አሳቢና ሰብዓዊነትን የተላበሰ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም በጁንታው የጥፋት ቡድን ይደርስባቸው የነበረውን ጫና ተቋቁመው የትግራይንም ሆነ የኢትዮጵያን ህዝብ ነጻ ለማውጣት ያደረጉት ትግል የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ያስቀመጡትን አቅጣጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ተግባራዊ እንዲያደርገው ጠይቀዋል።