ጠንካራ ሕብረ ብሔራዊ ሥርዓት ለመገንባት ወጣቱ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ተመላከተ - ኢዜአ አማርኛ
ጠንካራ ሕብረ ብሔራዊ ሥርዓት ለመገንባት ወጣቱ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ተመላከተ
ሀዋሳ ህዳር 22 2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ ጠንካራ ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ ወጣቱ አንድነቱን በማጠናከር የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አንዳለበት ተመላከተ።
የ15ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ ተከብሯል።
በዓሉ በፓናል ውይይት በተከበረበት ወቅት የደቡብ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፌ ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ ኢትዮጵያ ታላቅ ራዕይ የሰነቀች ሌሎች የዓለም ሃገራት ያልታደሏቸው ተፈጥሮዊና ባህላዊ ትውፊቶች ባለቤት ናት ብለዋል።
በተለያየ ጊዜ የመጡ የመንግስት አደረጃጀቶች ለባህላዊ ትውፊቶች በአግባቡ ትኩረት ባለመስጠታቸው ፀጋዎቹ ጎልተው ካለመውጣታቸው ባሻገር ለተለያዩ ችግሮች መነሻ እስከመሆን መድረሳቸውን ገልጸዋል።
ይህንን በማረም ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓት መገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ይህ ዕውን እንዲሆን ወጣቶች ግንባር ቀደም ትሳትፎ ማደረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በተለይ የወጣቱ ተሳትፎ ከግል ይልቅ ሃገራዊና ህዝበዊ ጥቅም በሚያስቀደም፣ አንድነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ሀገሪቱ ያላት የተፈጥሮ ጸጋዎቿ ጎልቶ በመውጣት የህዝቦቿን ጥቅም ያስከበረ እንዲሆን የተዛነፉ የታሪክ ትርክቶች በማስተካለል አንድነታችንን ለማጠናከር ወጣቱ በዕውቀትና በስነምግባር የታነጸ ቁመና እንዲኖረው ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በበኩላቸው ወጣቶች በሃገረ መንግስት ግንባታ ሂደት በምክንያታዊነት መሞገት እንዲችሉ በስብዕናና ግብረ ገብ ግንባታ ላይ ትኩረት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ወጣቶች ከመንደር አስተሳሰብ ወጥተው ሃገራዊ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ቤተሰብ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ማህበረሰብ፣ የትምህርት ተቋማትና መንግስት በተቀናጀ መልኩ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ ቢሮው ዘንድሮ የስብዕና ግንባታ ማዕከላትን በግብአትና ሰው ሃይል በማጠናከር የታለመውን ዓላማ ሊያሳኩ በሚችል መልኩ ለማደራጀት ትኩረት መስጠቱን አቶ ሙስጠፋ ተናግረዋል።
ከተሳታፊዎች መካከል ከሃዲያ ዞን የመጣችው ወጣት ቤቴልሄም አሰፋ፤ ወጣቶች ጠንካራና አሳታፊ የፌዴራል ስርዓት ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ ሚናቸውን ሊያጎለብቱ ይገባል ብላለች።
በተለይ የተነገቡ ሃብቶችን ከሚያፈርስ አስተሳሰብና ስሜታዊነት በመቆጠብ ዴሞክራሲያዊና ሠላማዊ ትግል ማካሄድ ከወጣቱ የሚጠበቅ መሆኑን ነው የተናገረችው።
በሃገሪቱ የመጣውን የለውጥ ሂደት እንዳይሳካ ወጣቱ በማያውቃቸው ትርክቶች ከልማት እንዲወጣና ተስፋ እንዲቆርጥ የሚሠሩ ሃይሎች መኖራቸውን መገንዘቡን የተናገረው ደግሞ ከምዕራብ ኦሞ ዞን የመጣው ወጣት ፍቅሩ ወልቃባ ነው፡፡
ሃገሬን የምወድ ወጣት ነኝ የሚል ሁሉ ልብ ብሎ በማሰብና የሃገራችንን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ከሃሳብ ማመንጨት እስከ ተግባር ድረስ መሳተፍ ይጠበቅበታል ብሏል።
ወጣቱ በየአካባቢው ባለው አደረጃጀት በመሳተፍ ሚዛናዊ የሆነ አስተሳሰብ ማጎልበት እንዳለበት ያነሳው ወጣት ፍቅሩ በተለይ ሰላምን በመጠበቅ የተጀመሩ የልማት ዕቅዶች እንዲሳኩ የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል።
በዓሉ "የደቡብ ክልል የወጣት አደረጃጀት አመራሮች የወጣቶች ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ለህብረ ብሄራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ ነው የተከበረው።