ቀጥታ፡

የሕግ ማስከበር እርምጃው በተቀመጠው ጊዜ መጠናቀቅ የዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ ስጋቶች የሚያስቀር ነው - አምባሳደር ሂሩት ዘመነ

አዲስ አበባ ህዳር 22/2013 (ኢዜአ) የሕግ ማስከበር እርምጃው በተቀመጠው ጊዜ መጠናቀቁ በዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የነበሩ ስጋቶችን የሚያስቀር ነው ሲሉ በቤልጂየም የኢትዮጵያ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ገለጹ። 

'የህወሓት ቡድን' ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ሲወሰድ የቆየው የሕግ ማስከበር እርምጃ ሕዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም መጠናቀቁ በመንግስት መገለጹ ይታወቃል።

በቤልጂየም የኢትዮጵያ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ኤምባሲው ስለ ሕግ ማስከበር እርምጃው ከጅምሩ አንስቶ ለቤልጂየም መንግስትና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማስረዳት ስራ ሲያከናውን መቆየቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በተለይም ኤምባሲው በሚሸፍነው የአውሮፓ ኅብረት ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ስለ ዘመቻው በተከታታይ ማብራሪያ መሰጠቱንና ውይይት መካሄዱን ተናግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቤልጂየም ቆይታቸው ከአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬልና ከቤልጂየም አቻቸው ሶፊ ዊልመስ ጋር ተወያይተው ማብራሪያ መስጠታቸውን አስታውሰዋል።

በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የሕግ ማስከበር እርምጃው ወደ እርስ በእርስ ግጭት ያመራል፣ ቀጣናዊ ቀውስ ያስከትላል የሚሉ ስጋቶች እንደነበሩም ገልፀዋል።

ይሁንና መንግስት ባስቀመጠው ጊዜ የሕግ ማስከበር ስራውን ማጠናቀቁ ስጋቶቹን የሚያስቀር መሆኑን ነው አምባሳደር ሂሩት የገለጹት።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለተቸገሩና ለተሰደዱ የሠብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት አኳያ ላነሱት ሀሳብ መንግስት ለዜጎች ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ብሔራዊ ኮሚቴ አዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱ እንደተገለጸላቸው ተናግረዋል።

በሕግ ማስከበር ሂደቱ ወደ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው የመመለስና የማቋቋም ስራ በተቀናጀ መልኩ እንደሚከናወን እንዲገነዘቡ መደረጉንም አብራርተዋል።

 አምባሳደሯ የአውሮፓ ኅብረት መንግስት የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያወጣቸው  መግለጫዎች መሬት ላይ ያለውን እውነታ የማይወክሉ እንደነበሩም ገልጸዋል።

በተለይም ኅብረቱ የሕግ ማስከበር እርምጃውን በሁለት ሃይሎች መካከል የሚደረግ ጦርነት አድርጎ ያየው ነበር ያሉት አምባሳደሯ እውነታውን በማስረዳት ይህን እሳቤ እንደቀየረ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የልማት አጋር የሆነው የአውሮፓ ኅብረት የተጀመሩ ለውጦች እንዲቀጥሉ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ መስኮች ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት አለው ብለዋል።

በቤልጂየም የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን በሕግ ማስከበር እርምጃው ዙሪያ ሚዛናዊ ያልሆኑ ዘገባዎች ሲያቀርቡ እንደነበረና ይህም ከመንግስት በኩል ያለውን አቋም ካለማካተት የመጣ እንደሆነ አስረድተዋል።

በብሮድካስትና በሕትመት መገናኛ ብዙሃን ቃለ መጠይቅ በማድረግና ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት ዘገባዎቹ ሚዛናዊና ትክክለኛውን ምስል እየያዙ መምጣታቸውንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ኤምባሲው በቤልጂየምና በሉክሰምበርግ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የደረሰውን ጥቃትና የሕግ ማስከበር እርምጃውን አስመልክቶ ውይይት ማድረጉን አምባሳደሯ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያዊያኑም በራሳቸው ተነሳሽነት የሕግ ማስከበር እርምጃውን በተለያዩ ቋንቋዎች የማስረዳትና ሚዛናዊ ያልሆኑ መረጃዎች ሲወጡ ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው ብለዋል።

በኤምባሲውና በቤልጂየም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ እስካሁን ለሠብዓዊ ድጋፍ ከ100 ሺህ ብር በላይ መሰብሰቡንና ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውንም ገልጸዋል።

በቀጣይ ለሠብዓዊ ድጋፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር እንደሚዘጋጅ ነው አምባሳደር ሂሩት የጠቆሙት።

በቤልጂየም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ በ"ገበታ ለአገር" እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተለያዩ ድጋፎች ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

ኮሚዩኒቲው በኢትዮጵያ ጉዳይ ያለው አንድነትና አቋም በጎ የሚባል እንደሆነና በአገር ጉዳዮች በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ አክለዋል።

ኢትዮጵያዊያኑ አገሪቷ ንግድና ኢንቨስትመንት መሳብ በምትችልበት በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂና በሌሎች ዘርፎች ያላት አቅም በሚጎለብትበት ሁኔታም ቡድን አቋቁመው እየሰሩ ነው ብለዋል።

በቤልጂየም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ማኅበር ለማቋቋም በሂደት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

ኤምባሲው በሚሸፍናቸው አገራት ለሚገኙ ዲፕሎማቶች በቀጣይ መንግስት በሚወስዳቸው እርምጃዎች ዙሪያ ገለጻ እንደሚያደርግም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም