በስራ አካባቢዎች ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመከላከል ከአሰሪና ሠራተኛ ማኅበራት ጋር በቅንጅት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በስራ አካባቢዎች ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመከላከል ከአሰሪና ሠራተኛ ማኅበራት ጋር በቅንጅት ይሰራል
አዲስ አበባ ህዳር 22/2013 (ኢዜአ) ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመከላከልና ቫይረሱ በደማቸው ያለ ወገኖችን ለመደገፍ ከአሰሪና ሠራተኛ ማኅበራት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለፀ።
ቢሮው ዓለም አቀፉን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቀን ምክንያት በማድረግ በመዲናዋ ከሚገኙ ድርጅቶችና የአሰሪና ሠራተኛ ተወካዮች ጋር መክሯል።
የቢሮው ኃላፊው አቶ ተፈራ ሞላ የአሰሪና ሠራተኛ እንዲሁም የመንግስትን ሚና የሚያመላክት የኤች.አይ.ቪ መከላከል ፖሊሲ በማውጣት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ቢሮው እ.አ.አ በ2030 በሽታው አሳሳቢ የጤና ችግር እንዳይሆን ለማድረግ ከአሰሪና ሠራተኛ እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በመላው ዓለም 38 ሚሊዮን ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው እንደሚገኝና ከእነዚህም 26 ሚሊዮን ወይም 68 በመቶ ያህሉ አምራች ኃይል መሆኑን የተናገሩት የቢሮው የኢንዱስትሪ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ካሳ ስዩም ናቸው።
ይህን ታሳቢ በማድረግ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን በስራ ቦታ መከላከል የሚያስችል በቂ የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ የሚገኙ ትልልቅ ድርጅቶች ማዕቀፉን በመተግበር ጤናማ የስራ ከባቢ ለመፍጠር የኤች.አይ.ቪ ፈንድ በማቋቋም ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሰዎችን እየደገፉ ይገኛሉ ብለዋል።
አነስተኛና መካከለኛ አምራች ድርጅቶች ቫይረሱን በመከላከልና ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በመርዳት በኩል በትኩረት መስራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሰዎች መብቶች እንዲከበሩ ከአሰሪና ሠራተኛ ማኅበራት ጋር በትብብር መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡
በዚህም ቢሮው በአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ በትኩረት ሊሰራባቸው ከያዛቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመከላከልና ፈንድ በማቋቋም አሰሪና ሠራተኞች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ እንደሚሰሩ በምክክር መድረኩ የተገኙ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽኖችና የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽኖች ተወካዮች ገልፀዋል።
በዓለም ላይ በአሁኑ ወቅት 38 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ሲሆን ከ23 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የፀረ-ኤች.አይ.ቪ ሕክምና ይወስዳሉ።
የኤች.አይ.ቪ/ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከሰተ ከጎርጎሮሳዊያኑ 1980ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በዓለም ላይ እስካሁን 35 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው ሕይወታቸው ማለፉን መረጃዎች ያሳያሉ።
34ኛው የዓለም የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቀን በኢትዮጵያ "ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመግታት ዓለምአቀፋዊ ትብብርና የጋራ ኃላፊነት" በሚል መሪ ሃሳብ ለ33ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው።