በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት አሁንም የጤና ስጋት ነው - የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ ህዳር 22/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት አሁንም የጤና ስጋት ሆኖ መቀጠሉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ። 

ዓለም አቀፉ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን በኢትዮጵያ ለ33ኛ ጊዜ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዛሬ ተከብሯል።  

በዚሁ መርሃግብር ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት፤ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት አሁንም የአገር የጤና ስጋት ሆኖ ቀጥሏል።

በመሆኑም አጠቃላይ ህዝቡ ሁሉም ተቋማትና የሚመለከታቸው አካላት ስርጭቱን ለመግታት በትብብር አንዲሰሩ ጠይቀዋል።

አሁን ላይ የኮሮናቫይረስ ስርጭት የተስፋፋበት ወቅት በመሆኑ ድርብ ስራና ሃላፊነትን ይጠይቃል ሲሉም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።         

በአዲስ አበባ ከተማ፣ በጋምቤላ ክልል እና ከተሜነት በተስፋፋባቸው ሌሎች አካባቢዎች የኤች አይቪ ቫይረስ ስርጭት ጨምሯል ብለዋል ሚኒስትሯ።

በተጨማሪም በግንባታ ቦታዎችና ኢንዱስትሪ ፓርኮችም ተመሳሳይ የስርጭት መስፋፋት መኖሩን ጠቁመዋለ።     

ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች የህክምና ክትትል ማድረግና መድሃኒት በአግባቡ መውሰድ እንዳለባቸው መክረዋል።

ቫይረሱ በደማቸው የተገኘባቸውን ግለሰቦችና በቫይረሱ ምክንያት ወላጆቻውን ያጡ ህጻናትና አረጋዊያንን በመንከባከበ የኀብረተሰቡ ትብብር መጠናከር እንዳለበትም ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

ችግሩ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ባለመሆኑ የክልልና ፌደራል ባለድርሻ አካላት፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የኃይማኖት ተቋማትና የመገናኛ ብዙሃን ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።  

የፌደራል የኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ጽጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው "ኤች አይ ቪ ኤድስን በተመለከተ የተፈጠረው መዘናጋት" ቀላል የማይባል ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።     

ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በኤች አይ ቪ ኤድስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ75 በመቶ መቀነስ ሲገባው በ52 በመቶ ብቻ መቀነሱን መረጃዎች እንደሚያሳዩ ዳይሬክተሯ አክለዋል።   

የቫይረሱ ስርጭት በተለይም በልማት ቦታዎችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሚሰሩ ወጣቶች ላይ እየተባባሰ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካይ 14 ሺህ 800 ሰዎች በኤች አይ ቪ እየተያዙ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የቫይረሱ ስርጭትም 0 ነጥብ 9 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ666 ሺህ 200 በላይ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።   

የዘንደሮው ዓለም አቀፍ የኤድስ ቀን የ"ኤች አይ ቪን ለመግታት ዓለም አቀፍ ትብብር ለጋራ ኃላፊነት'' በሚል መሪ ሀሳብ ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም