ቀጥታ፡

የናፈቋቸውን ዘመዶቻቸው ለማግኘት በመምጣታቸው መደሰታቸውን ኤርትራውያን ገለጹ

አዲስ አበባ አምሌ 11/2010 ኤርትራውያን የናፈቋቸውን ዘመዶቻቸው ለማግኘት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ ሲቃ እየተናነቃቸው ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ና ኤርትራ ለ20 ዓመታት ከቆዩበት የጥላቻ ፖለቲካ ወጥተው ሰላማዊ ግንኙነት በይፋ የጀመሩ ሲሆን፤ይህን ሁኔታ  ተከትሎም የኢትዮጵያ አየር መንግድ ከአዲስ አበባ አስመራና ከአስመራ አዲስ አበባ የሚደርገውን ጉዞ ዛሬ ጀምሯል። አየር መንገዱ ዛሬ ባካሄደው በረራ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ 465 ተጓዥችን ወደ አስመራ ያጓጓዘ ሲሆን፤ በቦይንግ ድሪም ላይነር 787-9  አውሮፕላን 97 ኤርትራውያንን ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ አምጥቷል። ኤርትራውያኑ ቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢሚግሬሸንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ ሰራተኞች በባህላዊ የኢትዮጵያ ቡና አፈላል የታጀበ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ኢዜአ በአቀባበል ስነስርዓቱ ተገኝቶ ያነጋገራቸው ኤርትራውያን እንዳሉት፤ በሁለቱ አገራት መካከል ተከስቶ የነበረው ቁርሾ ኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተሰቦቻቸውን የማግኘቱን ሁኔታ የህልም እንጀራ አድርጎባቸው ቆይቷል። የተፈጠረውን ሰላም ተከትሎ ከዘመዶቻቸው ጋር ለመገናኘት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቸው በጣም ደስ እንዳሰኛቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም