በህግ ማስከበር ዘመቻው የተገኘው ድል ኢትዮጵያ የማትፈርስ ሀገር መሆኗን ያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በህግ ማስከበር ዘመቻው የተገኘው ድል ኢትዮጵያ የማትፈርስ ሀገር መሆኗን ያረጋገጠ ነው
ሀዋሳ፣ ህዳር 22/2013 (ኢዜአ) መከላከያ ሰራዊት በጁንታው ላይ በወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ የተገኘው ድል ኢትዮጵያ የማትፈርስ ሀገር መሆኗን በተጨባጭ ያረጋገጠ መሆኑን የሀዋሳ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ገለፁ።
ፅንፈኛው የህወሀት ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈፀም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሞከረው ሙከራ አሳፋሪ የሀገር ክህደት መሆኑን ነዋሪዎቹ ለኢዜአ አስታውቀዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ መንገሻ ፊጣሞ እንደገለጹት የጁንታው ቡድን የፈጸመው ተግባር ሀገሪቱን በማተራመስ ለውጭ ጠላቶች ጥቃት አሳልፎ መስጠትን አላማ ያደረገ ነው ፡፡
"ሰራዊቱ የተከፈተበትን ጥቃት በመመከት በጁንታው ላይ የተቀዳጀው ድል ኢትዮጵያ በጠላቶቿ ሴራ የማትፈርስ ሀገር መሆኗን ያረጋገጠ ነው" ብለዋል።
ድሉ ከሀገራዊ አንድምታው ባሻገር ኢትዮጵያን ለማጥቃት የሚቃጣ ማንኛውም የውጪ ኃይል ቢኖር የመመከት አቅም እንዳላት ያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል።
አቶ ማርቆስ ሳኩማ በበኩላቸው "የህግ ማስከበር ዘመቻው ሌሎች ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ጣልቃ ሳያስገባ የተከናወነ መሆኑ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ያስመሰከረ ነው" ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ያስመዘገበው ድል ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ሆነ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ክብር ያሳየና ትውልድ የሚያወሳው ተግባር እንደሆነ አስረድተዋል።
"ድሉ ንፁሀን ዜጎች ኢላማ ሳይሆኑ የተገኘ መሆኑ በጣም አስደስቶኛል" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሳራ ሙሉጌታ ናቸው።
የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰራዊቱ ያሳየው ድጋፍ የሌሎች የውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት ሳይኖር ድል ማድረግ እንዳስቻለው ተናግረዋል።
"በህግ ማስከበር ዘመቻው ያሳየነውን አንድነት ድህነትን ለማሸነፍ ልንጠቀምበት ይገባል" ብለዋል።