በፀሀይ ኃይል የሚሰሩ የክትባት መድሃኒት ማቀዝቀዣ መሳሪያዎች በመሰራጨት ላይ ናቸው - የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በፀሀይ ኃይል የሚሰሩ የክትባት መድሃኒት ማቀዝቀዣ መሳሪያዎች በመሰራጨት ላይ ናቸው - የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሐምሌ 11/2010 የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ላለባቸው አካባቢዎች የሚያገለግሉ ስድስት ሺህ በፀሀይ ኃይል የሚሰሩ የክትባት መድሃኒት ማቀዝቀዥ መሳሪያዎች በመሰራጨት ላይ መሆናቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። የማቀዝቀዣ መሳሪያዎቹ ለአደጋ ተጋላጭ እና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ላለባቸው የአገሪቷ ክፍሎች የሚኖሩ ህጻናት ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ የክትባት አቅርቦት እንዲኖራቸው ያግዛል። የማቀዝቀዣ መሳሪያዎቹ መንግስት በመደበው 31 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገዙ ናቸው። በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የጤና ተቋማት ውስጥ ከሚገኙት የክትባት ማቀዝቀዣ መሳሪያዎች መካከል 41 በመቶዎቹ በኬሮሲን፤ የተቀሩት ደግሞ በከፊል ኤሌክትሪክ የሚሰሩ ናቸው። በየጊዜው የሚያጋጥመው የኬሮሲን እጥረትና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር የክትባት መድሃኒቶች ጥራትና አቅርቦት ላይ አደጋ ደቅኖ ቆይቷል። አሁን በየጤና ተቋማቱ የሚሰራጩት ማቀዝቀዣዎች እነዚህን ችግሮች በመፍታት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናትን ህይወትና ጤና ከአደጋ ለመከላከል የሚያገዙ የክትባት መድሃኒቶችን ጥራት ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችሉ መሆናቸው ተመልክቷል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የአገልግሎቱን መጀመር አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ፤ የክትባት ማቀዝቀዣ መሳሪያዎቹ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት አለባቸው ለሚባሉ የጤና ጣቢያዎች እና የወረዳ ጤና ጽህፈት ቤቶች እየተሰራጩ መሆናቸውን ገልጿል። ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ከበደ ወርቁ እንደሚሉት የጤናውን ዘርፍ የአገልግሎት ሽፋን በማሳደግ ፍትሃዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ሰፊ ተግባራት በማከናወን ላይ ናቸው። "ከነዚህም መካከል የክትባት ማቀዝቀዣ መሳሪያዎቹ ግዥና ተከላ በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው" ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፤ ይህም ከመድሃኒት መጓጓዝ ጋር በተያያዘ የሚገጥምን የጊዜና የኃብት ብክነት በመቀነስ የአገሪቷን የክትባት ሽፋን መጠን እንደሚያሳድገው ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ የተመዘገበ ቢሆንም እድሜያቸው ከ12 አስከ 23 ወራት ከሆኑት ህጻናት መካከል መሰረታዊ የሚባሉትን ክትባቶች የሚያገኙት 38 ነጥብ 5 በመቶ ያህሎቹ ብቻ ናቸው። ይህንን ችግር ለማቃለል ከሚያስችሉት ስልቶች መካከል አንዱ የመድሃኒት ማቀዝቀዣ ሰንሰለት ስርዓትን ማጠናከር እንደሆነ ሚኒስቴሩ አስታውቋል። አሁን እየተሰራጩ ያሉት መሳሪያዎችም ችግሩን በማቃለል "የአገሪቷን የክትባት ሽፋን መጠን ያሳድገዋል" የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።