የአንድ ማዕከል የመካናይዜሽንና ግብዓት አቅርቦት አገልግሎት ለአምራቹ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአንድ ማዕከል የመካናይዜሽንና ግብዓት አቅርቦት አገልግሎት ለአምራቹ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው
አዳማ፣ ህዳር 22/2013(ኢዜአ) ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ከእርሻ ማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርት መሰብሰብ ድረስ የአንድ ማዕከል የመካናይዜሽንና ግብዓት አቅርቦት አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ገለጸ።
በአርሲና ምዕራብ አርሲ ዞን የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይጎዳ የመካናይዜሽን አገልግሎት አሰጣጥና የምርት አሰባሰብ ሂደት ያለበት ሁኔታ ተገብኝቷል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ክፍሌ ወልደማሪያም በወቅቱ እንደገለጹት የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ ኮርፖሬሽኑ 22 ኮምባይነሮች በማሰማራት ለአርሶ አደሩ የአጨዳ አገልግሎት እየሰጠ ነው።
በአርሶ አደሩ የኋላቀር የምርት አሰባሰብ 30 በመቶ የምርት ብክነት ይኖራል ያሉት አቶ ክፍሌ በቤተሰብ ደረጃ አንድ ሄክታር የደረሰ ሰብል ለማንሳት ከአስር ቀናት በላይ እንደሚፈጅ ተናገረዋል።
ኮርፖሬሽኑ በተመጣጣኝ ዋጋ የአጨዳ ኮምባይነሮችን በማቅረብ የአርሶ አደሩን ጊዜና ወጪ ከመቆጠብ ባለፈ የምርት ብክነትን በ25 በመቶ ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
አገልግሎቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ 23 ማዕከላት መክፈታቸውን ገልጸዋል።
በተያዘው የበጀት ዓመት ተጨማሪ አዳዲስ ሶስት ማዕከላት በምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ትግራይና አማራ ክልሎች በመክፈት የአንድ ማእከል አገልግሎት ተደራሽ እናደርጋለን ያሉት አቶ ክፍሌ በቀጣዩ አምስት ዓመት ተጨማሪ አስር የአንድ ማእከል አገልግሎት እንደሚከፈት አስታውቀዋል።
በተያዘው የበጀት ዓመት ከ300 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያና ፀረ አረም ኬሚካል ለማቅረብ አቅደን እየሰራን ነው ያሉት ደግሞ በኮርፖሬሽኑ የምርጥ ዘርና ደን ውጤቶች አቅርቦት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘነበ ወልደስላሴ ናቸው።
በአርሶ አደሩና በባለሃብቶች ጭምር የዘር ብዜት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው በተለይ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ጥራ ጥሬና የቅባት እህሎችን ጨምሮ 26 የሰብል ዝርያዎች እየተመረቱ ይገኛሉ ብለዋል።
በኮርፖሬሽኑ የመካናይዜሽን አገልግሎትና ኦፕሬሽን ዘርፍ ሃላፊ አቶ ፈለቀ በበኩላቸው በተያዘው የበጀት ዓመት 22 ኮምባይነሮች መገዛታቸውን ጠቅሰው ከእነዚህም ውስጥ 12 የሚሆኑት ወደ ሀገር በማስገባት በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ለአርሶ አደሩ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪ የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን የእርሻ ትራክተሮች ፍላጎትን ለማሟላት ባለሃብቶች ጭምር በማስተባበር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን አመራሮችና ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የአርሲ አሰላ የምርጥ ዘር ዝግጅት፣ በምዕራብ አሳሳ አርዳይታ ግብርና ማዕከል የሰብል አሰባሰብና የኮፈሌ ምርጥ ዘር ማበጠሪያን ጎብኝተዋል።