የህወሃት ጁንታ በሴፍትኔት የምናገኘውን ገቢ ይወስድብን ነበር - የአዲ ቀይህ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የህወሃት ጁንታ በሴፍትኔት የምናገኘውን ገቢ ይወስድብን ነበር - የአዲ ቀይህ ከተማ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21/2013 (ኢዜአ) “የህወሃት ጁንታ ከሴፍትኔት መርሃ -ግብር የምናገኘውን ገቢ ከመውሰዱም በላይ በግድ መዋጮ እንድንከፍል ያደርገን ነበር” ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲ ቀይህ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።
በህወሃት ጁንታ ላይ ሲደረግ የነበረው የህግ ማስከበር ዘመቻ የመከላከያ ሰራዊቱ የመቀሌ ከተማን ተቆጣጥሮ ዘመቻውን አጠናቋል።
ሰራዊቱ በቀጣይ የጁንታውን አባላት እያደነ ለህግ የማቅረብና ለዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይሆናል።
መንግስት የወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ የጁንታው ቡድን "እመራዋለሁ" ለሚለው የትግራይ ህዝብም ትልቅ እፎይታን የፈጠረ መሆኑን በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች እየገለጹ ይገኛሉ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲ ቀይህ ከተማ ነዋሪዎች እንደሚሉት የህወሃት ጽንፈኛ ቡድን ባለፉት ሁለት ዓመታት በሴፍቲኔት የታቀፉ ነዋሪዎችን የሚያገኙትን ገቢ በተለያየ ምክንያት ይወስድባቸው እንደነበር ገልጸዋል።
በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሴፍቲኔት ገቢያቸው ላይ እየተቀነሰ ይወሰድ እንደነበር አመልክተዋል።
በተጨማሪም ቡድኑ ላደራጃቸው ታጣቂዎች ህዝቡ ምግብ በግድ እንዲያዋጣ ያደርግ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ቡድኑ በግጭቱ ምክንያት ሸሽተው የሄዱ የአካባቢውን ነዋሪዎችን ንብረት እንደዘረፈም ነው የተናገሩት።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት አካባቢያቸውን ከተቆጣጠረ በኋላ ሰላማዊ ኑሮ መምራት መጀመራቸውንም ገልጸዋል ።
አሁን ላይ የአገር መከላከያ ሰራዊት አካባቢውን ከተቆጣጠረ በኋላ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።