ማህበሩ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 21/2013 (ኢዜአ) የሳቦና ላየን ኮንስትራክሽን ሪል እስቴት አክሲዮን ማህበር ለአገር መከላከያ ሠራዊት 100 ሰንጋ በሬዎች እና 150 በጎችን ድጋፍ አደረገ።
የአክሲዮን ማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ቶፊክ ከድር ድጋፉን በዛሬው እለት ለሰራዊቱ አበርክተዋል።
በድጋፍ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አክሲዮን ማህበሩ ለሠራዊቱ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በትግራይ ክልል በህግ ማስከበር ስራ ላይ ተሰማርቶ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ህዝቡ እንዲሁም ተቋማት እያደረጉት ያለው ድጋፍም የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ለሰራዊቱ የሚደረገው ህዝባዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክትል ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል።
በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የቅርስ ጥበቃና ሙዚየም ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ደሳለኝ ጋቼ ድጋፉን በመረከብ ለአክሲዮን ማህበሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በየደረጃው እያደረገ ያለው ድጋፍ ለሠራዊቱ ሞራል በመሆን ተልዕኮውን በአጭር ጊዜና በተሳካ ሁኔታ እንዲፈፅም አድርጎታልም ብለዋል።
ህብረተሰቡ የአገር ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ ላይ ላለው የአገር መከላከያ ሠራዊት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የሳቦና ላየን ኮንስትራክሽን ሪል እስቴት አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ቶፊክ ከድር ለአገር መከላከያ ሠራዊት 100 ሰንጋ በሬዎች እና 150 በጎችን ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
ድጋፉ በገንዘብ ሲተመን 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር መሆኑንም ገልፀዋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት የህግ ማስከበር ዘመቻውን በድል በማጠናቀቁ መደሰታቸውን ገልጸው በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል በጁንታው ሃይል ላይ የተሳካ የህግ ማስከበር ስራ ማከናወኑ ይታወቃል።