የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን ከለውጡ ዋዜማ እስከ ዛሬ ለውጡን የማደናቀፍ ተግባር በጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት - ኢዜአ አማርኛ
የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን ከለውጡ ዋዜማ እስከ ዛሬ ለውጡን የማደናቀፍ ተግባር በጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት
አዲስ አበባ፣ ህዳር 21/2013 (ኢዜአ) ለሕግ ማስከበሩ እርምጃ መዘግየት ምክንያት የሆኑ የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን ከለውጥ ዋዜማ እስከ ዛሬ ለውጡን የማደናቀፍ ተግባራት - በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አንደበት
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ እስከዛሬ ስላለው የጽንፈኛው ቡድን የሽብር እንቅስቃሴ ዘርዝረዋል።
በለውጡ ዋዜማ በርካታ ሰዎችን በግፍ ማሰር፣ በአንድ ጉድጓድ መቅበር፣ ማፈናቀል ከአንድ የሽብር ኮሌጅ የተመረቁ ሰዎች የሚያደርጉት ለውጡን ለማፈን የተሰሩ የሽብር ተግባራት ናቸው።
እርሳቸውን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችን መከታተል፣ መሰለልና ማስፈራራት፤ በመጨረሻም በኢህአዴግ ሊቀመንበርነት ሊመረጡ ጥቂት ቀናት ሲቀሩ የእስር ማዘዣ እስከማውጣት እንደነበር አስታውሰዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ።
መንግስት የሚመስሉ ቡድኖች ብዙ አሻጥሮችን ቢፈጽሙም ለውጡን ማስቆም አለመቻሉን አብራርተዋል።
ከታጠቀ ቡድን ጋር የሚደረግ ግጭት ሌላ እልቂት ስለሚያመጣ የቡድኑን በደል ትተን በይቅርታ፣ በፍቅርና በመደመር እንለፈው በሚል በደሉን አፍነን እርቅ፣ ሠላምና ፍቅር ብንልም ሰባኪዎች ናቸው የሚሉ ሃሳቦች እንደነበሩና በደካማ መንግስትነት ማስፈረጁን ገልጸዋል።
በቡድኑ ላይ ቀድሞ እርምጃ ያልተወሰደው ተቋማዊ ብቃት ያስፈልግ ስለነበረ፣ ጥንቅቅ ያለ የሃይል አሰላለፍ ትንተና ስላልነበረ፣ የሁኔታ ትንተናም ባለመሰራቱ ነው ብለዋል።
በተመረጡ ዕለት የወቅቱ የደህነንት ሹም ጥበቃዎችን ቤተ መንግስት ይዘህ አትገባም በሚል መከልከላቸውን፣ የቢሮው ቁልፍ በደህንነት ጠባቂዎች፣ የቤቱ ዋናው ቁልፍም በደህነት ሰዎች እጅ እንደነበር አስታውሰዋል።
'በዚህ ሁኔታ ውስጥ የአገሪቷን ብቻ ሳይሆን የራሴን ደህንነት የማስጠበቅ ቁመና ላይ አልነበርኩም' ብለዋል።
'ከቤተ መንግስት ማምለጥ በማይቻልበት ዘመናዊ እስር ቤት ያለሁ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበርኩኝ' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የመጀመሪያውን ወር ስራ በዚህ ሁኔታ ማሳለፋቸውን ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተመረጡ በኋላ ከሕዝብ ጋር ለመወያየት መርሃ ግብራት ቢወጡም በሁሉም ክልል እንዳይንቀሳቀሱና ከሕዝብ ጋር እንዳይወያዩ በደህንነት ተቋሙ ክልከላዎች ነበሩ ነው ያሉት።
ለአብነትም ወደ ሶማሌ ክልል ለመሄድ ቢታሰብም የደህነት ሹሙ 'አልሸባብ ሊገልህ ነው' በሚል ጉዞው መከልከሉን ተናግረዋል።
ያም ሆኖ ጉዞው ተደርጎ በመቀሌ ስብሰባ ተካሂዶ ከሕዝቡ ጋር መምከር መቻሉን አስታውሰው፤ ባልተጠበቀው የሕዝብ ድጋፍ ጁንታው መደናገጡን ገልጸዋል።
ከደህንነት መዋቅሩ ሰዎች ጋር ከእስር የተፈቱ ሰዎችን መልሶ በማሰርና እስረኞችን በመፍታት መሰል አለመግባባት በኋላም ከረር ያለ ፀብ ውስጥ መገባቱን፤ የደህንነት አመራሩን ለማንሳት ጥናት ተደርጎ የደህንነት ተቋሙን ሹምና ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ መነሳታቸውን አውስተዋል።
ሹሞቹ ግን የደህንነት መሳሪያዎችን ይዘው መቀሌ መግባታቸውን፣ የደህንነት ተቋሙም የቤተሰብ ማህበር እንጂ ትክክለኛ የደህንነት ተቋም እንዳልነበረ ነው ያስታወሱት።
ከሰኔ 16 ጥቃት በኋላም የደህንነት ተቋሙ ተፈትሾ በርካታ የግድያ መሳሪያዎችና ትጥቆች መኖራቸው እንደታወቀ ተናግረዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱም ለቀጣይ ዓመታት ማስተካከል በሚከብድ መልኩ ከዋናው መስሪያ ቤት እስከ ዕዝና ብርጌድ የሰው ሃይል አመራሩ በትግራይ ተወላጆች የተሞላ እንደነበር ገልጸዋል።
ለአብነት በጄኔራል ደረጃ 60 በመቶ፣ በሌተና ጀኔራል 40 በመቶ፣ በሜጀር ጀኔራል 45 በመቶ፣ በብርጋዴል ጄኔራል 40 በመቶ፣ በኮሎኔል 58 በመቶ፣ በሌተናል ኮሎኔል 66 በመቶ፣ በሻለቃ 53 በመቶ በአንድ አካባቢ ሰዎች የተያዘ እንደነበር ይፋ አድርገዋል።
ይህን የመከላከያ ሠራዊት ስሪት ለማስተካከልና ለማመጣጠን እስከ 10 ዓመት የሚፈጅ መሆኑ ጉዳዩን ከባድ እንዳደረገውም ገልጸዋል።
አቅም ያለው አመራር ከአንድ አካባቢ ከትግራይ ብቻ እንዲወጣ ተደርጎ መሰራቱ ለማንም እንደማይጠቅም ተናግረዋል።
በስልጣን ደረጃ ሲፈተሽም 80 በመቶ በመከላከያ ተቋሙ አመራር የሚሰጡ ሃይሎች ከትግራይ መሆናቸውን፣ በዕዝ ደረጃም አዛዥና ምክትል አዛዥ መቶ በመቶ ከትግራይ እንደነበሩ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በክፍለ ጦር፣ በሜካናይዝድ መቶ በመቶ፣ በእግረኛ ክፍለ ጦር 80 በመቶ፣ በሜካናይዝድ ብርጌድ 85 በእግረኛ ብርጌድ 80 በመቶ በትግራይ ተወላጆች ቁጥጥር ስር እንደነበር፤ በመከላከያ ስልጠና ተቋማት 85 በመቶ በትግራይ መያዙን ተናግረዋል።
ይህን የተዛባ አወቃቅር የትግራይም ሌላውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም የድርሻውን ብቻ ማግኘት ያለበት የሕገ መንግስቱ መልክ ያላት ኢትዮጵያን መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
መከላከያው የተገነባው መቶ በመቶ ከሕገ መንግስቱ በሚጻረር፣ ሠራዊቱ ለፓርቲ ዘብ መቆም እንዳለበት በሚያትት፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከሌለ ኢትዮጵያ እንደሌለች በሚሰብክ ሰነድ እንደነበርም ተናግረዋል።
ቡድኑ መዋቅሩን በመጠቀም በየቦታው ግጭቶችን በመቀስቀስ ንጹሃንን ያስጨፈጭፍ እንደነበረ ለአብነትም በሲዳማ ክልል ወላይታ ሲጨፈጨፍ በቦታው የነበሩ ኣዛዦች እጅ እንደነበረበት ገልጸዋል።
በመዋቅሩ ያሉ ግለሰቦችን ማንሳት ሲጀመር የደህነትና የመከላከያ ተቋም ስሪት ለሁለት ዓመት ተኩል ዋና ዋና ግጭቶችን በመቀስቀስ ሕይወት እንዲቀጠፍ፣ ንብረት እንዲወድም ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
ከለውጡ በኋላ በኢትዮጵያ 114 ግጭቶች መከሰታቸውን በዚህም በኦሮሚያ 37፣ በአማራ 23፣ በቤኒሻንጉል 15፣ በአዲስ አበባ 15፣ በጋምቤላ ሰባት ግጭቶች መከሰታቸውንና ከግጭቶቹ ጀርባም የቡድኑ እጅ እንደነበረበት አብራርተዋል።
በዚህም መንግስት ስራው በጦርነት ማልቀስና መቅበር ሆኖ በተቀናጅ መንገድ ስራውን እንዳይሰራ ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በፋይናንስ፣ ሚዲያና ኔትወርክ በመጠቀም የብሄርና የሃይማኖት ግጭት እንዲፈጠር፣ የተጋመደ ሕዝብ እርስ በእርስ እንዲጠራጠርና አብሮ እንዳይኖር መደረጉንም ገልጸዋል።
በሁሉም ክልሎች ግጭቶች ቢኖሩም በትግራይ ብቻ እንዳልነበረ፤ በተመሳሳይ ክልል ከክልል ጋር ግጭቶች የነበሩ ሲሆን ትግራይ ግን ከማንም ክልል ጋር አለመጋጨቱን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በርካታ የመንግስትና የፓርቲ የስራ ሃላፊዎች ሰዎችን ለመግደል ሙከራ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ከለውጡ በኋላም ከጄኔራል እስከ ሻለቃ በትግራይ ተወላጆች ብልጫ የተያዘውን ቦታ ወደ 26 በመቶ፣ በዕዝ ደረጃ 100 በመቶ የነበረውን ወደ 25 በመቶ፣ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር 50 በመቶ፣ እግረኛ ክፍለ ጦር ከ80 ወደ 40፣ እግረኛ ብርጌድ ከ80 ወደ 40 በመቶ ቀስ በቀስ ዝቅ መደረጉን ገልጸዋል።
ይሁንና ከተቀነሱት መካከል አንድም ሰው የጡረታ ጊዜው ሳይደርስ የወጣ መኮንን እንደሌለና ከዚህ በፊት እንደነበረው ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ጡረታ የማስወጣት ተግባር እንዳልነበረ አስታውቀዋል።
ለውጥ ሲደረግ ከአገር መከላከያ ሲሰናበት የነበረ የሠራዊት አመራር ወደ ክልል እየሄደ ሌላ ጦር ማደራጀት መጀመሩንም ተናግረዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ በታችኛው አመራር ላይ መንግስታዊ ስልጠናዎች ተሰጥተው መከላከያ ከፓርቲ ወገንተኝነት እንዲፀዳ ተሰርቷል፤ የኢትዮጵያን አንድነትና ሕልውና ለመጠበቅ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ውስጣዊ ለውጥ ተደርጓል።
አገራዊ ዘመቻ የሚሰራ ልዩ ጦር መቋቋሙን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቡድኑ በማያውቀው መንገድ መደራጀቱንና ይህ አየር ሃይልና ልዩ ጦርም የሕግ ማስከበር ስራውን በብቃት መወጣቱን ተናግረዋል።
የንጹሃንን ጥቃት በተመለከተም መከላከያ ሠራዊቱ በየትኛውም ከተማ አንድም ዜጋ ያልገደለ ጀግና ሠራዊት መሆኑን አንስተዋል።
መንግስት ሃላፊነት ስለሚሰማው ሕግ ለማስከበር ከባድ መሳሪያ ወይም ሮኬቶች መጠቀም እንዳልተፈለገ ገልጸዋል።
እኛ ከሌለን አገር አትኖርም የሚሉ እንደነበሩ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኢህአዴግ ከፈረሰ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚለው መርዘኛ አስተሳሰብ መክሸፉንም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በፋይናንስ፣ በዴሞክራሲ ተቋማት አሳሪ ብሎም ከሕግ ማዕቀፍ ጋር የተያያዙ አሰራሮችን ማሻሻያ በማድረግ በለውጡ ከፍ ያሉ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም ምርጫ ቦርድ፣ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የሽብር ሕግ፣ የሚዲያ አዋጅ፣ የኢንቨስትመንት አዋጅ፣ የንግድ ሕግ፣ የግልግል ዳኝነት ሕግ፣ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አዋጅ፣ የዲፕሎማሲ ፖሊሲ እንዲሻሻሉ መደረጉን አውስተዋል፤ ጎረቤት አገራትንም ለአብሮነታቸው አመስግነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሚሳኢል ያለው ትግራይ ከልል በመሆኑ ትጥቁ ከክልሉ እንዳይወጣ ሴራቸውን በመሸረብ ማስወጣት እንዳልተቻለ ገልጸዋል።
የቡድኑ ፍላጎት ቀድሞውንም ለውጡ መጣ አልመጣም የአገሪቷ አቅም እዛው እንዲቀር ታስቦ የተሰራ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ የነዳጅ ዴፖም እዛው እንዲገነባ መደረጉን ተናግረዋል።
ለዚህም ሕግ የማስከበር ስራው ጊዜ ያስፈልገው ነበር እንጂ ዘግይቶ አልነበረም ብለዋል።
የጥፋት ቡድኑ ይህን ሁሉ አድርጎ አልሳካ ሲለው ጥቅምት 24 ስልክ፣ ኤሌክትሪክና መገናኛ አጥፍቶ በየቦታው በሚሊሻ ከቦ፣ ቄስና ሽማግሌ በመላክ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ ያልታወቀ ግፍ በሰሜን ዕዝ ላይ መፈጸሙን ተናግረዋል።
ከግፍም በላይ ደግሞ ሬሳ ለይተው አሰቃቂ ድርጊት ፈጽመዋል ነው ያሉት።
ከሮኬት ጥቃት ጋር ተያይዞም በአንዳንድ የትግራይ ከተሞች ሚሳኤል ማብላያ ስፍራዎች በከተሞች ተከማችተው ስለነበር ያልተመቱት ከተሞችን ከጥፋት ለመጠበቅ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየጦር ግንባሩ በመሰለፍ አኩሪ ስራ የሰሩ የጦር መኮንኖችና ጄኔራሎችንም አድንቀዋል።
የልዩ ጦሩን ተልዕኮና ጀግንነትም በበዛ አድናቆት ገልጸውታል። ጀግኖች ባይኖሩ ኖሮ አሁን ካለንበት ሁኔታ አንደርስም ነበር ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ድጋፍ የላቀ እንደነበር ተናግረዋል።
የጦር ወንጀለኞች፣ አገር ከሃዲዎችና የዘር ማጥፋት ፈጻሚዎችን ለሕግ የማቅረብ ስራ ይከናወናል፤ የታሰሩትን ነጻ ለማውጣት፣ የተሰረቀውን ለማስመለስም ይሰራል ብለዋል።
ቀጣዩ ስራ ወንጀለኞችን ለቅሞ ለሕግ ማቅረብ እንደሆነ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ 'የጽንፈኛው ሃይል አባላት ያፈኗቸውን ሰዎችና ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ከመቀሌ ሸሽተው አገረ ሠላም ይገኛሉ' ብለዋል።