በትግራይ የመንግስት ቀጣይ ሥራ ክልሉን መገንባት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ የመንግስት ቀጣይ ሥራ ክልሉን መገንባት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 21/2013 (ኢዜአ) በትግራይ የመንግስት ቀጣይ ሥራ ክልሉን መገንባት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ ልዩ ስብሰባውን አካሂዷል።
በምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በትግራይ ክልል ከተካሄደው ህግ ማስከበር በኋላ ቀጣዩ ስራ የክልሉን መሰረተ ልማትና ሌሎች ስራዎች ማከናወን ይሆናል ብለዋል።
የክልሉ ህዝብ እስካሁን በጁንታው ተፅእኖ ስር ወድቆ ሳይፈቱለት የነበሩትን ችግሮች በማቃለል የተሰደዱትን ዜጎች መልሶ የማቋቋም ስራ ይከናወናል ብለዋል።
የተሰደዱ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ የመመለስና የማቋቋም ሥራ ለማከናወን ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙንም ገልጸዋል።
ለዜጎች በሚደረገው ድጋፍ ለመተባበር ፍላጎት ያላቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ለሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት መንግስት በሩ ክፍት መሆኑንም አመልክተዋል።
የትግራይ ክልልን ለመገንባትና ህዝቡን ለመደገፍ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
የህወሓት ጁንታ እና የትግራይ ህዝብ የተለያዩ በመሆናቸው ህብረተሰቡ የትግራይ ተወላጆችን ማግለል እንደሌለበትና ጥበቃ ሊያደርግላቸው እንደሚገባም በድጋሜ አሳስበዋል።
በትግራይ ክልል ፖለቲካዊ ሁኔታን አስመልክቶ በሚኖሩ ውይይቶች የፌደራል መንግስቱ ግንኙነት የሚኖረው ሕጋዊ ከሆኑ የትግራይ ክልል ፓርቲዎች ጋር ብቻ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በተያዘው ዓመት በሚደረገው አገራዊ ምርጫ የትግራይ ህዝብ "ፈልጎ እና ወዶ በሚመርጠው" አካል የሚተዳደር ይሆናል" ብለዋል።