የመከላከያ ሠራዊት በህወሃት ቡድን ላይ የተቀናጀው ድል ለኢትዮጵያዊያን ልዩ ቀን ይዞ የመጣ ነው --የምስራቅ ወለጋ አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሠራዊት በህወሃት ቡድን ላይ የተቀናጀው ድል ለኢትዮጵያዊያን ልዩ ቀን ይዞ የመጣ ነው --የምስራቅ ወለጋ አስተዳደር
ነቀምቴ ህዳር 21/2013 (ኢዜአ) ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በከሀዲው የህወሃት ጁንታ ቡድን ላይ በወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ የተጎናጸፈው ድል ለኢትዮጵያዊያን ልዩ ቀን ይዞ የመጣ መሆኑን የምስራቅ ወለጋ ዞንና የነቀምቴ ከተማ አስተዳደሮች አሰታወቁ።
አስተዳደሮቹ መከላከያ ሰራዊት መቀሌን መቆጣጠሩን አስመልክተው የተሰማቸውን ደስታ ለኢዜአ ገልጸዋል።
የምሥራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሥመራ ኢጃራ እንደገለጹት የህወሃት ጁንታ ቡድን ሀገሪቱን ባስተዳደረበት 27 አመት የራሱን አሸባሪ ቡድን በማደራጀትና በሁሉም ክልሎች በማሰማራት ዜጎችን ለአፈና፣ ለእስራትና ለግድያ ሲዳርገና የህዝብ ሀብት ሲዘርፍ ቆይታል።
ከለውጡ በኋላም መቀሌ በመመሸግና የተንኮል ሴራውን በማስፋት ንጹሀን ዜጎችን በመጨፍጨፍና በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በማድረስ የሀገር ክህደት ወንጀል መፈጸሙን ተናግረዋል።
"ቡድኑ የፈጸመው ተግባር የዞኑን ጨምሮ መላው የሀገሪቱን ህዝብ አስቆጥቷል" ብለዋል ።
የመከላከያ ሠራዊቱ የህግ የበላይነትን ለማስከበር በቡድኑ ላይ በወሰደው እርምጃ የተጎናጸፈው ድል የትግራይን ጨምሮ መላውን ህዝብ ለመጨረሻ ጊዜ ከግፍ አገዛዝ ያላቀቀ መሆኑን ተናግረዋል ።
"ድሉ ለኢትዮጵያዊያን አዲስ ቀን ይዞ የመጣ ነው " ሲሉም ገልጸውታል።
በዞኑ አንዳንድ ወረዳዎች ቡድኑ ያደራጃቸው የኦነግ ሸኔ ተላላኪዎች በመኖራቸው ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም አድኖ በመያዝ ለሕግ ማቅረብ እንደሚጠበቅበት አስገንዘበዋል።
ህዝቡ የልማት ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ አቶ በሪሶ ተመስገን በበኩላቸው ሠራዊቱ ያስመዘገበው ድል የጁንታውን እኩይ ሴራና ዓለማ ያከሸፈና ወደ መቃብር የሸኘ መሆኑን ተናግረዋል።
"ቡድኑ ሀገሪቱን በደም ለቅልቆ ከደሙ ነጻ ለመምሰል የተለመደ የሀሰት ትርክቱን ቀጥሎበታል" ያሉት ከንቲባው መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም የኢትዮጵያ ሕዝብን የካደ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
መከላከያ ሰራዊት በቡድኑ ላይ የተቀናጀው ድል በተለይም የትግራይ ሕዝብ ከጭቆና ነፃ የወጣበትና ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በመሆን ከድህነት ወደ ብልጽግና፣ ከመበታተን ወደ አንድነት እንዲመለስ መሰረት የጣለ መሆኑን አስታውቀዋል ።
"ድሉ ለኢትዮጵያዊያን ልዩ ቀንና ተስፋ ይዞ የመጣ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
የከተማው ሕዝብ በተገኘው ድል በመደሰት ከመንግሥት ጎን በመቆም በከተማው የሚገኙ የሕወሐት ጁንታ ተላላኪዎችን በማጋለጥ ለሕግ እንዲያቀርብ ከንቲባው ጠይቀዋል ።
በትግራይ የተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጥበብ በተሞላበትና በሰውና በልማት ድርጅቶች ላይ ጉዳት ሳይደርስ በመጠናቀቁ ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የነቀምቴ ከተማ የልዩ ኃይል አዛዥ ኮማንደር ግርማ አብዲሣ ናቸው ፡፡