ቀጥታ፡

የህወሓት ጁንታ የተጀመረው ለውጥ እንዳይቀጥል የውስጥ ኃይል በመጠቀም ለማደናቀፍ ሲጥር ቆይቷል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21/2013 (ኢዜአ) የህወሓት ጁንታ መንግስት በተቀናጀ ሁኔታ የጀመረውን ለውጥ እንዳያስቀጥል የውስጥ ሃይል በመጠቀም ችግር ሲፈጥር መቆየቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ገለፁ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባ ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስብሰባው ተገኝተው የምክር ቤቱ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም የጁንታው ቡድን ተላላኪዎች በመንግሥት ውስጥ ሆነው ችግር ይፈጥሩ እንደነበር ተናግረዋል።

በአገሪቷ የተለያዩ ቦታዎች ግጭት፣ መፈናቀልና ግድያዎች እንዲደረጉ ኔትወርካቸውን በማስፋት ሲሰሩ መቆየታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የጁንታው አባላት በአንድ በኩል ግጭቶችን እየፈጠሩ፤ በሌላ በኩል ሠላም አስከባሪ ሆነው ይታዩ ነበር ነው ያሉት።

ከለውጡ ወዲህ በአገሪቷ 113 ግጭቶች መከሰታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በአብዛኞቹ ቀደም ሲል ጁንታው በደህንነት መዋቅሩ ያስቀመጣቸው ከሃዲ ኃይሎች እጅ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የምክር ቤቱ አባላት መንግሥት ጁንታው ሕገ-መንግስትና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በመጣስ በትግራይ ክልል ምርጫ ከማካሄድ ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የፈፀመውን ተግባር በመጥቀስ ቡድኑ በአሸባሪነት እንዲፈረጅ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም