የትኛውም አገር የህወሃት ጁንታ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመውን አይነት ጥቃት ቢገጥመው አይታገስም - ጠ/ሚ አብይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
የትኛውም አገር የህወሃት ጁንታ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመውን አይነት ጥቃት ቢገጥመው አይታገስም - ጠ/ሚ አብይ አህመድ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 21/2013 (ኢዜአ) "የትኛውም አገር የህወሓት ጁንታ በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመውን አይነት ጥቃት ቢገጥመው ፈጽሞ አይታገስም" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው።
የህወሓት ጁንታ ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው በማታውቀው መንገድ የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ አስነዋሪ ጥቃት በመፈጸም "የእናት ጡት ነካሽነቱን" አሳይቷል ብለዋል።
በጥቃቱ የገደላቸውን የሠራዊቱን አባላት እንዳይቀበሩ በማድረግም ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ያፈነገጠ አረመኔያዊ ድርጊት መፈጸሙን ተናግረዋል።
ይህን ካለመገንዘብ የተወሰኑ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባላት ሕግ የማስከበሩ እርምጃ ቆሞ ድርድር እንዲደረግ ፍላጎት አሳይተው እንደነበር አስታውሰዋል።
ነገር ግን የትኛውም አገር የህወሓት ጁንታ የፈጸመውን አይነት አስነዋሪ ድርጊት ቢገጥመው ፈጽሞ ሊታገስ አይችልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስትም ከዚህ አንጻር የአገርን ሉዓላዊ ሕልውናና የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውም አይነት ሙከራ እንደማይታገስ ተናግረዋል።
በሕግ ማስከበር ዘመቻው የጎረቤት አገራት ላደረጉት መልካም አበርክቶም ምስጋና አቅርበዋል።