ቀጥታ፡

የብልጽግና ፓርቲ መፈጠር የጁንታውን ረጅም የቁማር እጆች እንዲቆረጡ አድርጓል ... ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2013(ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲ መፈጠር የህወሓት ጁንታ ረጅም የቁማር እጆች እንዲቆረጡ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አባላት ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ  ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች  ሰፋ ባለው ማብራሪያቸው የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን አባላት በኢትዮጵያ በሁሉም፣ ከሁሉም፣ ለሁሉም የሆነ ተቋም ይገንባ ሲባል በታቃርኖ ይቆሙ እንደነበር ተናግረዋል።

'አፋር፣ ሶማሌና ሌሎችም እንዴት ከእኛ እኩል ድምጽ ይሰጣሉ' የሚል የኢትዮጵያዊያንን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ከንቱ አካሄድ እንደነበራቸውም ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብልጽግና ፓርቲ መመስረት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ብልሽት የፈወሰ ትልቁ ክስተት እንደነበረ ነው የተናገሩት።

ብልጽግና ሲፈጠር የጁንታው ቡድን በፖለቲካው መድረክ ያላቸው የቁማር እጅ እንዲቆረጥ ማድረጉንም ጠቅሰዋል።

"ለኢትዮጵያ ትልቁ ድልም የብልጽግና ፓርቲ መፈጠር ነበር" በማለት ነው የገለጹት።

ብልጽግና እነሱ እንደሚሉት አሃዳዊ ሳይሆን ለኢትዮጵያ እውነተኛ የፌዴራል ስርዓት እየፈጠረ ያለ የፖለቲካ ድርጅት መሆኑን ም አስታውቀዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ሁሉም ብሔረሰቦች በቋንቋቸውና በባሕላቸው ተከብረው "እምዬ ኢትዮጵያ" ብለው ተከባብረው በአንድነት የሚኖሩባትን አገር በሚገነባ ኃይል የሚመራ ድርጅት መሆኑንም አክለዋል።

ፓርቲው አንዱን ዝቅ አንዱን ከፍ፣ የአንዱ ቋንቋ እንዲታይ የአንዱ እንዲጠፋ የሚፈልግ እንዳልሆነም ተናግረዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ሁሉም ሕዝቦች በእኩልነት የሚሳተፉባቸውን ተቋማት ለመገንባት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ጥቅምን ማስከበር የሚቻለው በኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን ለጁንታው ኃይል ለማስረዳት እንደተሞከረና የመገንጠል ሃሳብ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌለው ተደጋጋሚ ምክረ ሃሳብ ተሰጥቷቸው እንደነበርም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም