ቀጥታ፡

የህወሓት አጥፊ ቡድን በለውጡ ማግስት ንፁሃንን በግፍ በመግደልና በጅምላ በመቅበር አገራዊ ስጋት ለመፍጠር ሞክሯል

አዲስ አበባ ህዳር 21/2013 (ኢዜአ) የህወሓት ጁንታ በለውጡ ማግስት ንፁሃን ዜጎች በግፍ እንዲገደሉ በማድረግ በጅምላ በመቅበር አገራዊ ስጋት ለመፍጠር መሞከሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

የአገሪቷን ከለውጡ ማግስት እስከ አሁናዊ የፖለቲካ ሁኔታም ገለፃ እያደረጉ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በለውጡ ማግስት የጁንታው ቡድን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች እንዲፈናቀሉ፣ በርካታ ንፁኃን ዜጎች በመግደልና በጅምላ በመቅበር ሰፊ አገራዊ ስጋት ለመፍጠር ሞክሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከለውጡ በፊትም የኦነግን ዓርማ በገፍ በማሳተምና ዓርማውን የያዙ ሰዎችን የኢሬቻ በዓል በሚከበርበት ስፍራ በማስገባት ንጹኃን ዜጎችን ለማፈን ይጠቀም እንደነበረም አንስተዋል።

ዓርማ የሌለውን ሰንደቅ ዓላማም እንዲሁ ንጹሃን ዜጎችን ለማጥፋትና ለማሳቀቅ ሲጠቀምበት እንደነበር ተናግረዋል።

በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበረው ቡድን ዜጎችን በማሳዘን ለውጥ እንዳይመጣ ለማድረግ ይሞክር እንደነበር ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

በለውጡ ሂደት በመሪዎች ላይ ክትትል ማድረግ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ እንዲሁም እስከ የእስር ማዘዣ ማውጣት የደረሰ አስጨናቂ የደህንነት ክትትል ሲደርግ እንደነበር ተናግረዋል።

የጁንታው ቡድን ባይሳካለትም የኢህአዴግ ግንባር ሊቀመንበር በሚመረጥበት ወቅትም የሚፈልጉትን ሰው ለመምረጥ ያልፈነቀሉት ድንጋይ እንዳልነበረ አስታውሰዋል።

የለውጡን መሪ በማስወገድ መንግስት ያልሆነ ግን የሚመስል ኃይል ለማስቀመጥ ፍላጎት እንደነበርና እኛ የምንፈልገ ሰው አገር ካልመራ በመቃብራችን ላይ ነው እስከ ማለት ደርሰው እንደነበርም አብራርተዋል።

ከለውጡ በኋላም በአዲስ አስተሳሰብ ቂም፣ በቀልና ጥላቻን በመተው በይቅርታ እንሻገር፤ አቃፊ አገረ መንግስት እንገንባ በሚል የተሻለ ሃሳብ ለማራመድ ተሞክሮ እንደነበር ገልጸዋል።

የጁንታው ኃይል ዋል አደር ብሎም በስብከት አገር አትመራም፤ ደካማ መንግስት ነው ያለው በሚል እሳቤ ለውጡ በተፈለገው መንገድ እንዳይመጣ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

ከለውጡ በኋላም በደሎችን በመርሳት በመደመር መርህ፣ በይቅርታና በፍቅር እንለፍ በማለት ከመጠፋፋት ፖለቲካ መውጣት እንዲቻል ያልተጠቀሙበት ነገር ግን ሰፊ ዕድል ተሰጥቶ እንደነበረ አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም