በትግራይ ክልል በተካሄደው ህግ ማስከበር አንድም ሰላማዊ ሰው ሳይጎዳ በጥንቃቄ የተከናወነ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል በተካሄደው ህግ ማስከበር አንድም ሰላማዊ ሰው ሳይጎዳ በጥንቃቄ የተከናወነ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
አዲስ አበባ ህዳር 21/2013 (ኢዜአ) የአገር መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል ባደረገው ህግ ማስከበር አንድም ሰላማዊ ሰው ሳይጎዳ በጥንቃቄ መከነወኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባውን በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በምክር ቤቱ በመገኘት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የህወሃት ቡድን የተለያዩ ፕሮፖጋንዳዎችን እየነዛ ቢሆንም የአገር መከላከያ ሰራዊት ሰላማዊ ዜጎች ሳይጎዱ ኦፕሬሽኑን ማከናወኑን ገልጸዋል።
መከለከያ ሰራዊቱ በጥንቃቄና ሰብአዊነት በተሞላው ስነ ምግባር ህዝብና ተቋማት ሳይጎዱ የተጀመረውን የሰላም ማስከበር ተግባር በድል ማጠናቀቁን ተናግረዋል።
በዘመናዊ መንገድ የተገነባው የመከላከያ ልዩ ሃይልና አየር ሃይል ግዳጁን በብቃት ተወጥተዋል ብለዋል።
የአገር መከላከያ ሰራዊት በዚህ ኦፕሬሽን አንድም ሮኬትና ሚሳኤል አለመተኮሱን አረጋግጠዋል።
የህወሃትን ጁንታ ለማንበርከክና የሚጠቀምባቸውን መሳሪያዎችና ምሽጎች ለማፈራረስ ዘመናዊ ድሮኖችን በመጠቀም በህዝብ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መደረጉንም ገልጸዋል።
የህወሃት ጁንታ ቀደም ሲል በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ለነበሩት ግጭቶችና የእርስ በርስ ግዲያዎች እጁ ነበረበት ሲሉም ለምክር ቤት አባላት አብራርተዋል።
ጁንታው በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የብሔር፣ የሃይማኖት ግጭት እንዲነሳ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን በማስታወስ በአጠቃላይ በ113 ግጭቶች ላይ እጁ ነበረበት ብለዋል።
በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት እንዲፈፀም አድርገዋል ነው ያሉት።