የህወሓት ጁንታ በሀገሪቷ ለውጥ ለማምጣት ሲንቀሳቀስ የነበረውን ሃይል ለመግደል፣ ለማፈንና ለማስፈራራት ብዙ ጥሯል- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
የህወሓት ጁንታ በሀገሪቷ ለውጥ ለማምጣት ሲንቀሳቀስ የነበረውን ሃይል ለመግደል፣ ለማፈንና ለማስፈራራት ብዙ ጥሯል- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ
አዲስ አበባ ህዳር 21/2013 (ኢዜአ) የህወሓት ጁንታ በአገሪቷ ለውጥ ለማምጣት ሲንቀሳቀስ የነበረውን የለውጥ ሃይል ለመግደል፣ ለማፈንና ለማስፈራራት ብዙ ጥሯል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትርር አብይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ ማግስት ጀምሮ በከባድ ፈተና ውስጥ ማለፋቸውን አስታውሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ወቅታዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎች ማብራሪያ በመስጠት ላይ ናቸው።
በኢትዮጵያ ለውጥ ለማምጣት የነበረውን አስቸጋሪ ሂደት ወደኋላ መለስ ብለው በማስታወስ ለምክር ቤቱ አባላት አብራርተዋል።
ለውጡን እውን ለማድረግ በተለይ የለውጥ ሃይሉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ማለፉንም አስረድተዋል።
በለውጡ ሂደት የህወሓት ጁንታ የለውጡን ሃይል ለመግደል፣ ለማፈንና ለማስፈራራት ብዙ ጥረት ማድረጉንም አስታውሰዋል።
እርሳቸውን ጨምሮ የለውጡን ሃይሎች፤ የህወሓት ቡድን አሁን ካደረገው ጦርነት ባልተናነሰ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አስገብቷቸው እንደነበርም ገልጸዋል።
ለውጡን ለማምጣት በነበረው ሂደት 'የህወሓት ቡድን ሊገድለን እንደሚችል እየዛተብን ስለነበር በቪዲዮና በፅሁፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግሉን እንዲያስቀጥል መልእክት አዘጋጅተን አስቀምጠን ነበር ሲሉ ተናግረዋል።
የህወሓት የተደራጀ ቡድን በለውጡ መሪዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ በማውጣት 'ወደ እስር ቤት ሊያስገባን ተዘጋጅቶም ነበር' ሊሉም ጠቅሰዋል።
በነበረው የአመራር ለውጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡም በኋላ ስራቸውን እንዳይሰሩ በርካታ ማስፈራሪያዎችና መሰናክሎች ገጥመዋቸው እንደነበረም አውስተዋል።
በጊዜው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዋስትና መሆን ይቅርና ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ህልውናም በህወሓት ቡድን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ ገልጸዋል።