በሀገር ክህደት ወንጀል የተጠረጠሩ የጦር መኮንኖች ቤት በተደረገ ኦፕሬሽንና ብርበራ በግለሰብ እጅ መያዝ የሌለባቸው የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር ክህደት ወንጀል የተጠረጠሩ የጦር መኮንኖች ቤት በተደረገ ኦፕሬሽንና ብርበራ በግለሰብ እጅ መያዝ የሌለባቸው የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ህዳር 21/2013 (ኢዜአ) በሀገር ክህደት ወንጀል የተጠረጠሩ የጦር መኮንኖች ቤት በተደረገ ኦፕሬሽንና ብርበራ በግለሰቦች እጅ መያዝ የሌለባቸዉ የጦርመሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ፡፡
ከሀዲ ጁንታው የህውሃት ቡድን እንደ ሀገር ብጥብጥና ቀውስ ለማድረስ አልሞ ረጅም አመታት በመዘጋጀት ጥቃት ማድረስ ከጀመረበት እለት አንስቶ በተደረጉ ፍተሻዎችና ብርበራዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የተለያዩ የጦርመሳሪያዎች መያዛቸው ይታወቃል፡፡
በዚህም የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ከሀገር መከላከያ ሚንስቴር ጋር በመተባበር በሀገር ክህደት ወንጀል የተጠረጠሩ የጦር መኮንኖች ቤት በተደረገ ፍተሻ ከፋተኛ ጉዳትና ኪሳራ ማድረስ የሚችሉ የጦር መሳሪያዎች የጦር ሜዳ መነፅሮች፣ ጅፒኤስ፣ በሳተላይት የሚሰሩ ስልኮች፣ ቦንቦች፣ክላሽንኮቭ፣ብሬን፣ለእኩይ ተግባር ማስፈፀሚያ የሚውሉ የተቀየረው የሰራዊቱ የደንብ ልብስ እና ሌሎች በግለሰብ እጅ መያዝ የሌለባቸዉ መሳሪያዎች በፍተሻ ሊያዝ መቻሉ ተገልጿል፡፡
ፍተሻው አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችና የሀገሪቱ ቦታዎች የተካሄደ ሲሆን የተያዙ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎቹ በአዲስ አበባ ከተማና በተለያዩ የሀገሪቱ ቦታዎች ሽብር ለመፍጠርና ሀገርን ለማበጣበጥ ጁንታዉ የህወሓት የጥፋት ቡድንና ተላላኪዉ የኦነግ ሸኔ ሊጠቀሙባቸዉ እንደነበር እንደተደረሰበት ተጠቅሷል፡፡
በመከላከያ ሚንስቴር ከፍተኛ አመራሮች በነበሩ ግለሰቦች በህገ-ወጥ መንገድ ከተቋሙ ወደ ግለሰቦች እጅ እንዲገቡ የተደረጉ መሳሪያዎች ባይያዙ በተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ቀውስ ያስከትሉ እንደነበርም ነው የተጠቀሰው፡፡
በተደረገው ኦፕሬሽንና በህብረተሰቡ ጥቆማ ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለዉ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ መረጃ እየተጣራባቸው እንደሚገኝም ከፌደራል ፖሊስ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡