3ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ ዛሬ በአልጄሪያ ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
3ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ ዛሬ በአልጄሪያ ተጀምሯል
አዲስ አበባ ሀምሌ 11/2010 3ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ ዛሬ በአልጄሪያ ርዕሰ መዲና አልጀርስ ተጀምሯል። ውድድሩ በአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር አዘጋጅነት በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው ይህ ውድድር እድሜያቸው ከ14 እስከ 18 ዓመት ዕድሜ ባላቸው ስፖርተኞች መካከል የሚካሄድ ነው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ በስድስት ስፖርቶች የምትሳተፍ ሲሆን በአጠቃላይ ውድድሩ በ35 የስፖርት አይነቶች ይካሄዳል። አትሌቲክስ፣ ቦክስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ካራቴ፣ ብስክሌትና ጠረጴዛ ቴኒስ ኢትዮጵያ የምትሳተፍባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው። በየስፖርቶቹ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች ላለፉት ሶስት ወራት ልምምዳቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ አልጄሪያ ላቀናው ልዑካን አሸኛኘት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። በአሸኛኘት ስነ ስርአቱ የሁለቱ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች የልዑካን ቡድኑ የቡድን መንፈስ በማጎልበት የአገራችሁን ባንዲራ በክብር ከፍ በማድረግ ህዝባችሁን ለማኩራት በርትታችሁ ስሩ ብለዋቸዋል። የአሰልጣኞችና የአትሌቶች ተወካዮችም በበኩላቸው የተቻላቸውን ሁሉ ሰርተው የአገራቸውን ባንዲራ ከፍ በማድረግ ህዝባቸውን ለማኩራት ቃል ገብተዋል። 3ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ እስከ ሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ይቆያል። በሌላ በኩል የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር(አኖካ) ትናንት በአልጄሪያ ባደረገው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ሌሴቶ ከአራት ዓመት በኋላ የሚካሄደውን አራተኛውን የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ እንድታዘጋጅ ወስኗል። ከአራት ዓመት በፊት በቦትስዋና በተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ በቦትስዋና ርዕሰ መዲና ጋቦሮኒ ሲካሄድ ኢትዮጵያ 14 የወርቅ፣ 6 የብር፣ 7 የነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት አምስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። የመጀመሪያው የአፍሪካ የወጣቶች ጨዋታ ከስምንት ዓመት በፊት በሞሮኮ ርዕሰ መዲና ራባት መካሄዱ ይታወሳል።