በጁንታው መወገድ ዋነኛ ተጠቃሚ የሚሆነው የትግራይ ህዝብ ነው ... አቶ አሻድሊ ሃሰን - ኢዜአ አማርኛ
በጁንታው መወገድ ዋነኛ ተጠቃሚ የሚሆነው የትግራይ ህዝብ ነው ... አቶ አሻድሊ ሃሰን
አሶሳ፤ ሕዳር 20/2013(ኢዜአ) መቀሌ መሽጎ የነበረው የህወሃት ጁንታ መወገድ ዋነኛ ተጠቃሚ የሚሆነው የትግራይ ህዝብ ነው ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የሃገር መከላከያ ሠራዊት መቀሌን በመቆጣጠሩ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ይህንኑ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ህወሃት ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ ተቀምጦ እርስ በርስ ሲያጋጭ ነበር ብለዋል።
ይህን ለማሳካት የሀገሪቱን ሕዝቦች በብሄር በመከፋፈልና ግጭት በመቀስቀስ ስልጣኑን ለማስቀጠል ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ እንዲፈጠር ማድጉን አመልክተዋል።
በጠረፍ አካባቢ የሚገኙ ክልሎችን ደግሞ በሞግዚት በማስተዳደር የተፈጥሮ ሃብታቸውን መዝረፉን ያስረዱት አቶ አሻድሊ፤ ክልሎቹ በአግባቡ እንዳይለሙም አድርጓ ብለዋል።
ህወሃት በትጥቅ ትግል ያካበተውን ሴራ ለውጡን ለማደናቀፍ እንደተጠቀመበት አመልክተው፤ በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች ንጹሃን እንዲጎዱና ንብረት እንዲወድም ማድረጉን አስረድተዋል።
ጁንታው ያጣውን ስልጣን መልሶ ለማግኘት መቀሌ በመመሸግ ህጻናትን ጭምር ለጦርነት በመመልመል ጥረት ማድረጉን አስታውሰዋል።
ህግን ለማስከበር በተካሄደው ዘመቻ የሃገር መከላከያ ሠራዊት የመጨረሻ ምሽጋቸው መቀሌን መቆጣጠሩ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘመቻው በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ድጋፍ አድርጓል።
የትግራይ ህዝብን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ለመነጠል የጥፋት ቡድኑ ተግቶ ሲሰራ እንደነበር ያወሱት አቶ አሻድሊ፤ በጁንታው መወገድ ዋነኛ ተጠቃሚ የሚሆነው የትግራይ ህዝብ ነው ብለዋል።
የትግራይ ህዝብ በመቀሌ የመሸጉትን የጁንታው አባላት አጋልጦ ለሃገር መከላከያ መስጠት አለበት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የጥፋት ቡድኖቹ ለህግ ከቀረቡ በኋላ ህዝቡ እፎይታ ያገኛል ነው ያሉት።
የጁንታው አባላት ፍጻሜያቸው ሲቃረብ ያወደሙትን የአክሱም አየር ማረፊያ፣ መንገዶችን፣ ድልድዮችን እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት በቅርቡ እንደሚጀመር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በትግራይ ለተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ያስታወቁት አቶ አሻድሊ፤ ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አለን ብለዋል።