በአዲስ አበባ ከተማ በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ ዋና ከተማ አሶሳ ስም ትምህርት ቤቶች ተሰየሙ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከተማ በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ ዋና ከተማ አሶሳ ስም ትምህርት ቤቶች ተሰየሙ

ህዳር 20/2013 (ኢዜአ) ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመርሀግብሩ እንደገለፁት የትምህርት ቤቶቹ ስያሜ ዋናው አላማ የቀጣዩ ትውልድ የብሄር ብሄረሰቦችን እሴት እና ባህል ተገንዝበው በአብሮነት እና በአንድነት እርስ በእርስ ለመቀራረብ መሆኑን ተናግረዋል።
ዛሬ ስያሜ የተሰጣቸው ትምህርት ቤቶች የክልሎቹን ባህል፣ማንነት እና ታሪክ በሚያንፀባርቁ መንገድ እንዲገነዘቡ እና እንዲደራጁ ይደረጋል ብለዋል ወ/ሮ አዳነች ።
ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ፣የአዲሰ አበባ ምክር ቤት አፈጉባዔ ወ/ሮ ዘርፈሽዋል ንጉሴ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታደለ ተረፈ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በትምህርት ቤቶቹ በመገኘት በይፋ ሰይመዋል።
የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሀመድ እና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታደለ ተረፈ የሁሉም ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ በክልላቸው ካሉ ከተሞች ስም ትምህርት ቤት መሰየሙ እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል።
አያይዘውም የክልላቸውን ባህል ፣ማንነት እና ታሪክ የሚገልጹ ሙሉ ቤተመጻሕፍት እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በክልሎቹ ሙሉ ወጪ ለመሸፈን ቃል ገብተዋል ።
ዛሬ ስያሜ ያገኙት ትምህርት ቤቶች በጥቂት ቀናት ተጠናቀው ለትምህርት ዝግጁ እንደሚሆኑም ተገልጿል ።
ምንጭ-የአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪ