የህወሃትን ጁንታ ለህግ ከማቅረብ ጎን ለጎን የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ይሰራል--- ብልጽግና ፓርቲ - ኢዜአ አማርኛ
የህወሃትን ጁንታ ለህግ ከማቅረብ ጎን ለጎን የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ይሰራል--- ብልጽግና ፓርቲ
አዲስ አበባ ህዳር 20/2013 (ኢዜአ) የህወሃትን ጁንታ አድኖ ለህግ ከማቅረብ ጎን ለጎን በህግ ማስከበሩ ሂደት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እንደሚሰራ ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ።
ፓርቲው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ላይ የተቀዳጀውን ድል አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም የህወሓት ጁንታ ለውጡን ለማደናቀፍ እስካሁን ያልሞከረው የጥፋት መንገድ የለም ብሏል።
ቡድኑ በአገሪቷ ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ የዴሞክራሲ ግንባታ ሥራ እንዳይሳካና የአገሪቷን ሰላምና ጸጥታ የሚያናጉ ሥራዎችን ሌት ከቀን ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሷል።
ጁንታው የጥፋት መንገድ መከተሉ እየታወቀም በለውጥ አመራሩ የሰላም ጥሪ ቢቀርብለትም ሳይቀበል መቅረቱን ብልጽግና በመግለጫው አስታውሷል።
ቡድኑ በሴራው ቀጥሎ የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም የእናት ጡት ነካሽና ከሃዲ መሆኑንም በተግባር አረጋግጧል ብሏል።
በመሆኑም በዚህ ከሃዲ ቡድን ላይ የሀገር መከላከያ በወሰደው የአገር ህልውና እና ህግ ማስከበር ዘመቻ በድል ማጠናቀቁን ገልጿል።
ድሉን በማስመልከትም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን ደስ አለችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
በህግ ማስከበር ሂደቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እንደሚሰራም ፓርቲው በመግለጫው አረጋግጧል።
ጁንታው ያፈራረሳቸውን መሰረተ ልማቶች መልሶ በመገንባት አገልግሎት እንዲሰጡ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቋል።
የፓርቲው ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።
ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ሁሌም ያሸንፋል
በአገራችን ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል የህዝቡን እውነተኛ የዴሞክራሲ ጥያቄ ለመመለስ እና ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው የመንግስት ስርዓት ለመገንባት ተጨባጭ ለውጥ በማስፈለጉ በህዝብ ግፊት የተቀጣጠለውና በፓርቲያችን ሳቢነት እውን የሆነው የለውጥ ሂደት ለኢትዮጵያዊያን ብሩህ ተስፋን ፈንጥቋል፡፡ የህወሓት ጸረ ህዝብ አጥፊ ቡድን ኢትዮጵያዊያን የራሳቸው ያደረጉትን ለውጥ ለማደናቀፍና አገርን ለመበታተን ያልሞከረው የጥፋት መንገድ አልነበረም፡፡
ይህ ህገ ወጥ ቡድን በአገራችን ጠንካራ ህብረብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንዳይሳካ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለእኩይ ተግባሩ ማስፈጸሚያ የሚሆኑ አካላትን በማደራጀትና በማስታጠቅ የዜጎች መፈናቀል፣ ግድያ፣ የንብረት ውድመት እና ሌሎችም የአገሪቱን ሰላምና ጸጥታ የሚያናጉ በርካታ ተግባራትን በመፈጸም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በተለይም በአገራችን የለውጥ አመራሩ ኃላፊነት ከተረከበ በኋላ ጁንታው ራሱን ከፌዴራል ስርዓቱ ነጥሎ መቀሌ ከተማ ከመሸገ በኋላ በአንድ በኩል ለጦርነት እየተዘጋጀ በሌላ በኩል በፌዴራል መንግስት የሚወጡ ህጎችን፣ የሚሰጡ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎችን ባለመፈፀም በፌደራል መንግስቱ ላይ አፍራሽ መግለጫዎችን እስከማውጣት የደረሰ ተግባር ሲፈጽም ቆይቷል፡፡
የህወሓት ቡድን የአገራችን ህዝቦች ያነሷቸውን የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በወንድማማችነት እና በአንድነት መንፈስ ማረጋገጥ እንዲቻል በአገራዊ ለውጡ እንዲካተት ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በርካታ ተደጋጋሚ ጥረቶች የተደረጉ ቢሆንም ሁሉንም የሰላም ጥሪዎች እየረገጠ የጦርነት ነጋሪት ሲጎስም ቆይቶ የኢትዮጵያዊነት ተመሳሌት የሆነውን ህብረብሄራዊ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከጀርባው በመውጋት የእናት ጡት ነካሽ ከሃዲ ቡድን መሆኑን በተግባር አረጋግጧል፡፡
አይደለም በአንድ አገር ልጆች ላይ በጠላት አገርም ላይ ተደርጎ በማይታወቅ መልኩ የመከላከያ ሠራዊታችንን አመራሮችና አባላት በማንነታቸው በመለየት ፍጹም ባልገመቱበት ሁኔታና ጊዜ በበርካታ የሰሜን ዕዝ ካምፖች የተቀናጀ ጥቃት በመሰንዘር የውድ ሠራዊታችን አባላት ህይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድል፣ ትጥቆች እንዲዘረፉ እና እንዲወድሙ አድርጓል፡፡ በማይካድራ ከተማ ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ ዜጎችን አስቀድሞ በማንነታቸው በመለየት ከ700 በላይ ንጽሃን ለፍቶ አዳሪ ዜጎችን ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲጠፋ በማድረግ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል፡፡
የአገር መከላከያ ሠራዊታችን ይህንን ገደብ ያለፈ ጥቃትና የውንብድና ተግባር ለመመከትና የአገራችንን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስቀጠል የህግ ማስከበር እርምጃ ሲወስድ ቆይቶ የትግራይ ክልልን ከጁንታው አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ነጻ አድርጓል፡፡ ሠራዊታችን በተቀዳጀው ድል መላው የአገራችን ህዝቦች እንኳን ደስ አላችሁ እያልን በተለይም በጁንታው አገዛዝ ስር ከፍተኛ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጽእኖ ስር ለነበረው የትግራይ ህዝብ እንኳን ለዚህች ታሪካዊ ቀን አበቃችሁ ለማለት እንወዳለን፡፡
የአገር መከላከያ ሠራዊታችን አባላት ባልተጠበቀ ሁኔታ የህወሓት ጁንታ ቡድን ከጀርባ ጥቃት ቢሰነዝርባችሁም ራሳችሁን በፍጥነት እንደገና በማደራጀት ራስን ከመከላከል አልፋችሁ የአገራችንን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስከበር ለከፈላችሁት መስዋዕትነትና ላሳያችሁት ጀግንነት ታላቅ ምስጋና እያቀረብን አገራችንን ከዚህ ከሃዲና አረመኔ ቡድን በማጽዳት ቀና ብለን እንድንራመድ ስላደረጋችሁን የተሰማንን አገራዊ ክብር ስንገልጽላችሁ በታላቅ ኩራት ነው፡፡
የአገራችን ህዝቦች በአንድነት፣ በመተሳሰብና በወንድማማችነት እንዳይኖሩ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ የቆየው የጁንታው ቡድን ላይመለስ ፈራርሷል፡፡ በመሆኑም ህብረ ብሔራዊትና የመተሳሰብና የአንድነት ምልክት የሆነች ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት በምናደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም በጁንታው የአገዛዝ ጫና ሥር የነበረው የትግራይ ህዝብ ግምባር ቀደም ተሳታፊና ተጠቃሚ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡
የወንጀለኛውን ጁንታ አባላት ከተደበቁበት አድኖ ለፍርድ ከማቅረብ ጎን ለጎን በህግ ማስከበር እርምጃው ሂደት ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አገራቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙና እብሪተኛው ጁንታ ያፈራረሳቸው የህዝብ መሰረተ ልማቶች በፍጥነት ተጠግነው ለአገልግሎት እንዲውሉ በልዩ ትኩረት የሚሰራ ይሆናል፡፡ የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና መላው የአገራችን ህዝቦች በትግራይ ክልል የህዝብ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ፣ የእለት ደራሽ ሰብዓዊ አገልግሎቶች በፍጥነት ደርሰው እንዲሰራጩና ህብረተሰቡ ወደ መደበኛ የእለት ተእለት ህይወቱ እንዲመለስ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የቻላችሁትን አስተዋጽዖ ሁሉ እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
ብልጽግና ፓርቲ
ህዳር 20 ቀን 2013 ዓ.ም.