ቀጥታ፡

ሰራዊቱ የተቀዳጀው ድል የሀገርና ህዝብ መከታነቱን በተግባር ያረጋገጠ ነው -- የበደሌ ከተማ ነዋሪዎች

መቱ/ፍቼ/ ነገሌ ህዳር 20/2013 (ኢዜአ) የሀገር መከላከያ ሰራዊት በፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ላይ በወሰደው እርምጃ የተቀዳጀው ድል የሀገርና ህዝብ መከታነቱን ያረጋገጠ ነው ሲሉ የበደሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በተመሳሳይ የፍቼና ነገሌ ከተሞች ነዋሪዎችም ሰራዊቱ ንጹን ዜጎች ሳይጎዱ በህወሃት ቡድን ላይ የተጎናጸፈው ድል ለበለጠ ሰላምና እድገት የሚያናሳሳ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይም የበደሌ ከተማ ነዋሪዎች የሀገር መከላከያ ሰራዊት በፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ላይ ለተቀዳጀው ድል የተሰማቸውን ደስታ ዛሬ በሰላማዊ ሰልፍ ገልፀዋል::

በሰልፉ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች እንዳሉት የመከላከያ ሰራዊቱ ባጭር ጊዜ ባስመዘገበው ድል ሀገሪቱን ከየትኛውም አደጋ መጠበቅ የሚያስችል ቁመናና ዝግጁነት እንዳለው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

ከሰልፈኞቹ መካከል የባለ ሶስት እግር ታክሲ አሽከርካሪ ወጣት በድሉ አያና በሰጠው አስተያየት መከላከያ ሰራዊት ፅንፈኛውን የህወሓት ጁንታን ለህግ ለማቅረብ በወሰደው እርምጃ  በአጭር ቀናት መቀሌን ጨምሮ ክልሉን መቆጣጠሩ እንዳስደሰተው ገልጻል።

"መከላከያ ሰራዊቱ በጁንታው ቡድን ላይ የወሰደው እርምጃ ለሀገርና ህዝብ ትልቅ ኩራት ነው " ያለው ደግሞ ወጣት ኑረዲን አባራያ ነው::

"ለሰራዊቱ ያለንን ደጀን ለመግለጽ ስናበረክት የነበረውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን" ብሏል።

የበደሌ ከተማ ከንቲባ አቶ ፀጋዬ ተሾመ በሰልፉ ላይ ባደረጉት ንግግር ሰራዊቱ በጠንካራ አመራር በህዝብ ላይ ጉዳት ሳይደርስ ድል መቀናጀቱ በእጅጉ የሚያስመሰግነው ነው።

ህብረተሰቡ ለመከላከያ ሰራዊቱ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ደጀንነቱን ማሳየቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የፍቼና ነገሌ ከተማ ነዋሪዎችም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ንጹሀን ዜጎች ሳይጎዱ በከሃዲው የህውሐት ቡድን ላይ የተጐናፀፈው ድል የሚያኮራና ለበለጠ ሰላምና እድገት የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸዋል ።

"ሰራዊቱ የተጎናጸፈው ድል የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና በህዝቦች   ከአፈናና ዘረኝነት አገዛዝ የተላቀቁበት ታሪካዊ ድል በመሆኑ እጅግ ኮርተናል" ሲሉ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል ።

"ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል የትግራይን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመነጠልና እንዲከፋው በማድረግ ተወጥሮ በነበረው የከሃዲው ሕውሐት ጁንታ ላይ የተገኘው ድል እጅግ አስደስቶናል" ብለዋል ነዋሪዎቹ።

ሰራዊቱ በወሰደው ህግ የማሰከበር ዘመቻ በትግራይ ህዝብ ላይ ጉዳት ሳይደርስ በመጠናቀቁ ኮርተናል ሲሉ ነዋሪዎቹ ለኢዜአ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም