ሠራዊቱ በህዝብ ላይ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስ መቀሌን መቆጣጠሩ አስደስቶናል- የወላይታ ዞን አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱ በህዝብ ላይ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስ መቀሌን መቆጣጠሩ አስደስቶናል- የወላይታ ዞን አስተዳደር
ሶዶ ህዳር 20/2013 (ኢዜአ) የሀገር መከላከያ ሰራዊት በወሰደው ህግ የማሰከበር እርምጃ በህዝብ ላይ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስ መቀሌን መቆጣጠር መቻሉ የወላይታ ህዝብና አሰተዳደር ደስታ ተሰምቶታል ሲሉ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አስታወቁ።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እንድሪያስ ጌታ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ጀምሮት የነበረውን ህግ የማስከበር ተግባር በድል በማጠናቀቁ የዞኑ ህዝብና አስተዳደር የተሰማውን ደስታ ገልጸዋል ።
"መከላከያ ሰራዊቱ የህወሀት የጥፋት ቡድኑን ለህግ ለማቅረብ በከፈለው መስዋዕትነት የአካባቢው ህዝብ ላይ ጉዳት ሳይደርስ በጥንቃቄ መቀሌን መቆጣጠሩ የዞኑን ህዝብና አስተዳደር አስደስቷል" ብለዋል።
ቡድኑ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ በርካታ እልቂት እንዲፈፀምና በታሪክ ይቅር የማይባል ጥፋቶች ሲፈጽም የነበረ መሆኑን የተናገሩት አስተዳዳሪው ቡድኑ የሚገባውን ቅጣት እንዲያገኝ መከላከያ ሰራዊቱ ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡
"በጽንፈኛው ቡድን ለዓመታት መብቱ ተነፍጎ የቆየው የትግራይ ህዝብ የጭቆና ቀንበሩ ከላዩ ላይ ስለተነሳለት ደስታ ተሰምቶናል" ጠቁመዋል።
የሶዶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዘካሪያስ ታደሰ በበኩላቸው "በመከላከያ ሰራዊቱ እየተወሰደ የሚገኘው ህግ የማስከበር ዘመቻ ኢትዮጵያ በጠላቶቿ እንደማትፈርስ ትልቅ ማሳያ ነው" ብለዋል፡፡
በመከላከያ ሰራዊት የተወሰደውን ሀገርን የማዳን ታሪካዊ ዘመቻ ለማገዝ ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ሲያሳይ ለነበረው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተገኘው ድል የእንኳን ደስ አለህ መልዕክት አስተላልፈዋል።