ሰራዊቱ የህግ ማስከበር ግዳጁን በፍጥነት እና በጥበብ ተወጥቶ ድል በማድረጉ ኮርተንበታል-- የመዲናዋ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሰራዊቱ የህግ ማስከበር ግዳጁን በፍጥነት እና በጥበብ ተወጥቶ ድል በማድረጉ ኮርተንበታል-- የመዲናዋ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ ህዳር 20 /2013 (ኢዜአ) የአገር መከላከያ ሠራዊት የህግ ማስከበር ግዳጁን በፍጥነት እና በጥበብ በመወጣት ድል በማድረጉ መደሰታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።
የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ትላንት አመሻሹ ላይ በሰጡት መግለጫ ሠራዊቱ በድል ታጅቦ የመቀሌ ከተማን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩን ይፋ አድርገዋል።
የኢዜአ ሪፖርተር በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ያነጋገራቸው ሰዎች እንዳሉት መንግስት የህወሃትን ጁንታ ወደ ሰላም ለማምጣት ብዙ ጥሯል።
የአገር ሽማግሌዎች፣ እናቶችና አባቶችም ጁንታው በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሲፈፅም የነበረውን በደል ይቅር በማለት ለሰላም እጁን እንዲዘረጋ ብዙ መለመናቸውን አስታውሰዋል ።
ሆኖም ቡድኑ ራሱን ለውጊያ ሲያዘጋጅ ቆይቶ በሰራዊቱ ላይ ያልታሰበ ጥቃት በማድረስ ክህደት በመፈፀሙ ሁሉንም አሳዝኗል ብለዋለ።
ከዚህ በኋላ ሠራዊቱ ጁንታው ያሰማራቸውን የጥፋት ኃይሎች ደምሰሶ ቡድኑ የመሸገባትን መቀሌ ከተማ በአጭር ጊዜ በመቆጣጠሩ ተደስተናል በሰራዊቱም ኮርተናል ብለዋል።
የድሉ ዋነኛ ተዋናይ የትግራይ ህዝብ እንደሆነ እንረዳለን ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ ከአፈናም ነፃ ወጥተዋል ሲሉ ተናግረዋል።
መንግስት ካደረገው ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ በኋላ የወሰደው እርምጃና የሠራዊቱን ተልዕኮ የመፈጸም ብቃት የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።
የህወሓት ቡድን ካለው የስልጣን ጥመኝነት የተነሳ "በአገር ዘራፊነቱ" ለመቀጠል ሲል በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ብዙ ግፍ መፈፀሙንም አስታውሰዋል።
የትግራይ ህዝብ ለዘመናት ሲያነሳው የነበረው የልማት ጥያቄ ተገቢ መልስ እንዲያገኝ የመገናኛ ብዙሀን ለክልሉ ህዝብ አይንና ጆሮ ሊሆኑ አንደሚገባ ጠቁመዋል።
የህወሃት ጁንታ ከተወገደ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና መረጋጋት፣ አብሮነት እየጠነከረ እንደሚሄድም ገልጸዋል።