ቀጥታ፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የእንኳን ደስ አላቸሁ መልዕክት መልዕክት አስተላለፈ

አዲስ አበባ ህዳር 20/2013 (ኢዜአ) የአገር መከላከያ ሰራዊት በትግራይ የሚካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ሶስተኛ ምዕራፍ በድል በማጠናቀቁ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የእንኳን ደስ አላቸሁ መልዕክት አስተላለፈ።

“የድል ሰንደቅ የሀገር አለኝታና ደጀን የህዝብ ልጅ የሆነው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን በተቀዳጀው ድል የተሰማንን ደስታ ሲገልፅ በከፍተኛ ኩራት ነውና እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን !!!” ብሏል።

“የመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን በሞራል፣ በሁለንተናዊ ድጋፎች ከጎኑ በመሆን ለተገኘው ድል ከፍተኛ ድርሻ አበርክታችኋል” ያለው ምክር ቤቱ፤ ድሉ የሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መሆኑን ገልጿል።

“የተመዘገበው ድል የሕዝባችን ህብረ ብሄራዊ ጠንካራ አንድነት በጋራ የመቆም ውጤት እና የመከላከያ ሰራዊታችን የሕገ መንግስት ታማኝነት ድል መገለጫ ነው” ብሏል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ጀግንነት፣ ምሳሌነት እና ቁርጠኝነት ለሀገሪቱ መፃዒ ጊዜ ትልቅ መሰረት እንደተከለ ምክር ቤቱ እንደሚገነዘብ አመልክቷል።

“ደስታውንና ድሉን እያጣጣምን በህብረ ብሄራዊ ፌዴራል ስርዓታችንና አብሮነታችንን የሚሸረሽሩ እኩይ ተግባራትን በተመሳሳይ መልኩ በጋራ እየተከላከልን አንድነታችን እና ክብራችንን አስጠብቀንና አጠናክረን ሀገራዊ ሁለንተናዊ ብልጽግና አጀንዳዎች ላይ በማተኮር የታላቅ ሀገር ባለቤትነታችንን በቀጣይ ድሎችም እናረጋግጣለን” ሲል ባስተላለፈው የደስታ መልዕክት መግለጹን ኢዜአ ከምክር ቤቱ ያገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም