የሀረሪና አማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደሮች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
የሀረሪና አማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደሮች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ
ሐረር/ባህርዳር ህዳር 21 /2013 (ኢዜአ) የሀገር መከላከያ ሰራዊት መቀሌን በመቆጣጠር ላስመዘገበው አንፀባራቂ ድል የሀረሪና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ ።
አቶ ኦርዲን በድሪ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ባስተላለፉት መልዕክት የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን መቀሌን ጨምሮ መላውን የትግራይ ክልል በመቆጣጠሩ የህዝብ አልኝታነቱን አሳይቷል፡፡
የተገኘው ድል ኢትዮጵያ ለጀመረችው ወደ ላቀ ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያሸጋግራት መሆኑን ተናግረዋል።
"መከላከያ ሰራዊታችን የተሰጠው ህግ የማስከበር ተልዕኮ አስደናቂ በሆነ ፍጥነት፣ ጽናትና አንፀባራቂ ጀግንነት መቀሌ ከተማን ጨምሮ መላው ትግራይን በመቆጣጠሩ በራሴ፣ በሀረሪ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ ስም የተሰማኝን ጥልቅ ደስታ እገለጿለሁ" ብለዋል ።
ለሰራዊታችን ያለንን የላቀ ከበሬታና አድናቆት ለመግለጽ እወዳለሁ " ያሉት ርዕሰ መሰተዳደሩ ለመላው የሀረሪና የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
በተመሳሳይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የመቀሌ ከተማን መቆጣጠሩን አስመልክተው ለመላው የአማራና የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ባስተላለፉት መልዕክት "የተገኘው ድል ስግብግቡን ጁንታ እራሱ በቆፈረው ጉድጓድ እየተቀበረ መሆኑን የሚያሳይ ነው" ብለዋል።
"ሀገር ለማፍረስ ቋምጦ የነበረው ጁንታ መቀበር የክልላችና የሃገራችን ህዝቦች የዘመናት የትግል ውጤት እውን እየሆነ መምጣቱን የሚያረጋግጥ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።
"ለድሉ መገኘት የመከላከያ ሰራዊታችን፣ የአማራ ልዩ ኅይልና ሚሊሻ አባላት በጋራ በፈጸሙት ተጋድሎ የመጣ ውጤት በመሆኑ ክብር ይገባቸዋል" ብለዋል።
"በመላ ህዝባችን የጋራ ተጋድሎ በተቀዳጀነው ወሳኝ ድል የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክቴን በራሴና በክልሉ መንግስት ስም አስተልፋለሁ "ሲሉ አስታውቀዋል።