የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መከላከያ መቀሌን ከጁንታው ነፃ ማድረጉን ተከትሎ ደስታቸውን እየገለፁ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መከላከያ መቀሌን ከጁንታው ነፃ ማድረጉን ተከትሎ ደስታቸውን እየገለፁ ነው
አዲስ አበባ ህዳር 20/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የአገር መከላከያ መቀሌን ትናንት ከጁንታው ታጣቂ ሃይል ነፃ ማድረጉን ተከትሎ ደስታቸውን እየገለፁ ነው።
በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች በየጎዳናዎች ሰንደቅ አላማ ይዘው የህወሃት ጁንታ በአገር መከላከያ ሰራዊት፣ በአማራ ልዩ ሃይልና ሚኒሻ አንዲሁም በህዝቡ ትብብር በመወገዱ ደስታቸውን እየገለጹ ነው።
"ጁንታው ይፈርሳል እንጂ ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ የኢትዮጵያ ካንሰር ተወግዷል፣ የጁንታው አባላትም እየተለቀሙ ለፍርድ ይቀርባሉ" ብለዋል በመልእክታቸው።
የህወሃት ጁንታ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ የሰራዊቱ አባላት ላይ ባደረሰው ያልታሰበ ጥቃት በርካቶችን አሳዝኖ አልፏል።
የጁንታውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት ሲያካሂደው የነበረው ህግ የማስከበር አርምጃም በትናንትናው እለት በመቀሌ ተጠናቋል።
በቀጣይ የጁንታው አባላት ከፖሊስና ህዝቡ ጋር በሚደረግ ትብብር እየታደኑ ለህግ እንደሚቀርቡ የአገር መከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም የህግ ማስከበሩ የመጨረሻ ምእራፍ በስኬት መጠናቀቁን ይፋ አድርገው የትግራይ ህዝብ ላደረገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም የጁንታው ታጣቂ ሃይል ያፈረሳቸውን መሰረተ ልማቶች መንግስት የተቻለውን ሁሉ ጥረት በማድርግ መልሶ እንደሚገነባ ቃል ገብተዋል።